አቶ ታዬ ደንደአ ወደ ኦዴፓ ጽሕፈት ቤት ተዛወሩ

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 9/2011) የፌደራል ጠቅላይ አቃቤህግ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆኑት አቶ ታዬ ደንደአ ወደ ኦዴፓ ጽሕፈት ቤት ተዛወሩ።

ለሶስት ወራት ከቆዩበት የፌደራል የሃላፊነት ቦታ ተነስተው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ኦዴፓ ማዕከላዊ ጽሕፈት ቤት  የሕዝብ ግንኙነት ክፍል በምክትል ሃላፊነት እንዲሰሩ መውሰኑን ለማወቅ ተችሏል።

አቶ ታዬ ደንደአ ከፌደራል መስሪያ ቤት ወደ ክልላዊ ፓርቲ ጽሕፈት ቤት እንዲዛወሩ የተደረገበት ምክንያት ባይታወቅም በአዲሱ የኦዴፓ መዋቅራዊ አደረጃጀት መሰረት መፈጸሙን የኢሳት የመረጃ ምንጮች ገልጸዋል።

አቶ ታዬ ደንደአ ለበርካታ ጊዜያት በህወሃት አገዛዝ አማካኝነት ለእስር የተዳረጉ ሲሆን በህዝባዊ ተቃውሞ ጠንካራ አቋም በመያዝ የሕወሃትን መንግስት በግልጽ ከሚያወግዙ የኦሮሚያ ክልል መንግስት  ባለስልጣናት አንዱ ነበሩ።

የኦሮሚያ ክልል ፍትህ ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ በነበሩ ጊዜ በአሜሪካን ድምጽ ሬዲዮ ቀርበው የህወሃትን አገዛዝ የተቃወሙበት ቃለመጠይቃቸው ለእስር ዳርጓቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ሊመጡ በዋዜማው ከእስር የተለቀቁት አቶ ታዬ ደንደአ በጠንካራ አቋማቸውና ጽናታቸው የሚጠቀሱ ናቸው።

አቶ ታዬ ደንደአ ወደ ፌደራል መንግስቱ በከፍተኛ የሃላፊነት ቦታ ከተቀመጡ ወዲህ ግን በአወዛጋቢ መልዕክቶቻቸው መነጋገሪያ ሆነው ቆይተዋል።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ሆነው ብቅ ያሉት አቶ ታዬ ደንደአ በተለይ በግል የፌስ ቡክ ገጻቸው በሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች ተቃውሞ ሲገጥማችው እንደነበረ ለማወቅ ተችሏል።

በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘ ለአንድ ወገን ያደሉና ሚዛናዊ ያልሆኑ መልዕክቶችን ማስተላለፋቸው በብዙዎች ዘንድ ስጋትንና ጥርጣሬን ያስከተለ ሆኗል።

በሃላፊነት ከተቀመጡበት ከፍተኛ ስልጣን ጋር በሚጣረስ መልኩ በዛቻና ማስፈራራት ላይ ያተኮረው ተከታታይ መልዕክታቸው ህዝቡን በለውጡ ያየውን ተስፋ እንዳያጨልመው በመስጋት መንግስት ጉዳዩን እንዲያጤነው በተለያዩ ወገኖች ግፊት ሲደረግ ቆይቷል።

የአቶ ታዬ ደንደአ ከፌደራል ባለስልጣንነት ወደ ክልል ፓርቲ ጽሕፈት ቤት መዛወር በፌስ ቡክ ከገቡበት ውዝግብ ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ የታወቀ ነገር የለም።

ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት የአቶ ታዬ ደንደአ የፌስ ቡክ መልዕክቶች የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግን አሰራር የሚጣረስ፣ ወገንተኝነትም የሚንጸባረቅበት መሆኑን በመረዳት በመንግስት በኩል የተወሰደ ርምጃ ነው።

አዲሱ ኦዴፓ ድርጅታዊ አቅሙን ለማጠናከር በሚል አቶ ታዬ ደንደአን ወደ ፓርቲው እንደወሰዳቸውም የሚገልጹ ወገኖች አሉ።

ኦዴፓ በአዳዲስ ተሿሚዎች ፓርቲውን የማጠናከር ስራ በማከናወን ላይ መሆኑንም የደረሰን መረጃ ያመለክታል።