አሜሪካና እንግሊዝ ከጋዜጠኛ ጀማል ካሾጊ ጋር በተያያዘ በሳኡዲ አረቢያ የተዘጋጀውን የኢንቨስትመንት ኮንፈረንስ ረግጠው ወጡ።
( ኢሳት ዜና ጥቅምት 08 ቀን 2011 ዓ/ም ) የሳኡዲ አረቢያ ንጉሳውያን ቤተሰቦችን የሚተች ጽሁፎችን በዋሽንግተን ፖስት እና በተለያዩ ታላላቅ ሚዲያዎች ላይ በማውጣት የሚታወቀው ጋዜጠኛ ካሾጊ የዛሬ አስራ አምስት ቀን ነበር ከጋብቻ ጋር በተያያዘ ጉዳይ ለማስፈጸም በቱርክ ኢስታምቡል በሚገኘው የሳኡዲ ኤምባሲ እንደገባ በዚያው የቀረው።
ያን ተከትሎ የቱርክ ባለሥልጣናት ካሾጊ በሳኡዲ አረቢያ መገደሉን ሲገልጹ እና ሳኡዲ አረቢያ ክሱን ስታስተባብል ቆይታለች።
በጉዳዩ ዙሪያ በተከታታይ የሚወጡ መረጃዎች ካሾጊ በቆንጽላ ጽህፈት ቤቱ በአሰቃቂ ሁኔታ መገደሉን እያመላከቱ መምጣታቸው ፤በሪያድ ላይ ዓለማቀፍ ተቃውሞና ጫና እንዲበረታባት አድርጓል።
እንደተባለው ሳኡዲ በግድያው እጇ መኖሩ ከተረጋገጠ ፣ከሪያድ ጋር በሀገር ደረጃ ያላቸውን ግንኙነት ለማጤን እንደሚገደዱ ካስጠነቀቁት ኃያላን መካከል አሜሪካና እንግሊዝ ዋነኞቹ ናቸው።
በጋዜጠኛ ካሾጊ ግድያ አጣብቂኝ ውስጥ የገባችው ሳኡዲ አረቢያ የቀረበባትን ክስ በተደጋጋሚ ብታስተባብልም፣ በየዕለቱ የሚወጡ ተከታታይ መረጃዎች በግድያው እጇ እንዳለበት የሚጠቁሙ ናቸው።