ከአዲስ አበባ ታፍሰው ጦላይ ታስረው ከነበሩት ወጣቶች መካከል 1 ሺህ 174ቱ ተለቀቁ

ከአዲስ አበባ ታፍሰው ጦላይ ታስረው ከነበሩት ወጣቶች መካከል 1 ሺህ 174ቱ ተለቀቁ
( ኢሳት ዜና ጥቅምት 08 ቀን 2011 ዓ/ም ) በቡራዩ ከተማ ከተፈጸመው ጭፍጨፋ እና እሱን ተከትሎ በተነሳ ተቃውሞ ከአዲስ አበባ ከተማ በርካታ ወጣቶች በጅምላ ተይዘው ጦላይ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከል ከአንድ ወር በላይ ታስረው መቆየታቸው ይታወቃል።
ፖሊስ ወጣቶቹ በጦላይ ስልጠና ሲከታተሉ መቆየታቸውን የገለጸ ሲሆን፤ ወጣቶቹ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ይህን ያህል ጊዜ በጦላይ መቆየታቸው የህግ ጥያቄ ሲያስነሳ ቆይቷል። ፖሊስ ወጣቶቹ ን”ሰላማችንን እንጠብቅ” የሚል ካናቲራ በማልበስ ዛሬ ማርፈጃውን ለቋቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በፓርላማ ማብራሪያ ሲሰጡ ከታሰሩት ወጣቶች ውስጥ 1 ሺህ 174ቱ እንደሚፈቱ እና ከባድ ወንጀል በፈጸሙ ወደ ሰማንያ በሚጠጉ ላይ ክስ እንደሚመሰረት ጠቅሰዋል።
ይሁንና የመዲናዋ ነዋሪዎች በጦላይ የታሰሩት ወጣቶች አሀዝ በጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ በፖሊስ ከተገለጸው በእጅጉ እንደሚልቅ እየተናገሩ ነው።
እስረኞቹ እንዲለቀቁ በርካቶች በማኅበራዊ ሚዲያው ዘመቻ ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወሳል።
በተያያዘ ዜና ትናንት ምሽት በፖሊስ የታሰሩት ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉ እና አቶ ሚካኤል መላዕክ ዛሬ ፍርድ ቤት መቀርበዋል። ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ “አዲስ አበባን የክፍለ ሃገር ልጅ አይመራትም እያሉ ቀስቅሰዋል፣ ማኅበር ለማቋቋም ሙከራ ሲያደርጉ ነበር ” በማለት ወጣቶችን በመቀስቀስ እና በማደራጀት ሲንቀሳቀሱ ነበር። ይህን ዓላማቸውን ለማሳካትም ከፍልስጤም ኢምባሲ ጋር ግንኙነት በመፍጠር ከኢምባሲ ሰዎች ጋር ይገናኙ ነበረ “ሲል ክስ አቅርቦባቸዋል።
ከተጠርጣሪዎቹ ጋር አባሪዎችን ጨምሮ ለመያዝም የሰባት ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ፖሊስ ጠይቋል። ፍርድ ቤቱም ፖሊስ የጠየቀውን የሰባት ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቅዶ ተለዋጭ የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ፖሊስ በጠበቃ አቶ ሄኖክ አክሊሉ እና አቶ ሚካኤል መላዕክ ላይ ያቀረበውን ክስ አስመልክቶ ዜጎች በማኅበራዊ ሚዲያ ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው።
ጠበቃ አቶ ሄኖክ አክሊሉ ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ የታሰሩ ወጣቶችን ጨምሮ ለበርካታ ዜጎች በነጻ ጥብቅና ሲቆም የነበረ ወጣት ነው።