የአዲስ አበባ ወጣቶች ከጦላይ ወታደራዊ ካምፕ ተለቀቁ

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 8/2011) ባለፈው ወር መጀመሪያ በጅምላ ታፍሰው ወደ ጦላይ ወታደራዊ ካምፕ ተወስደው የነበሩ ከ1ሺህ በላይ የአዲስ አበባ ወጣቶች ዛሬ መለቀቃቸው ተገለጸ።

ለወጣቶቹ ስልጠና ተሰጥቶ መለቀቃቸውን የገለጸው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ወደ ቤተሰቦቻቸው የማጓጓዝ ስራ መጀመሩን አስታውቋል።

ከፍተኛ ተቃውሞ ያስነሳውና ህገመንግስታዊ መብቶችን የጣሰ ነው የተባለው የአዲስ አበባ ወጣቶች እስርን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ያለአግባብ የታሰሩ ከነበሩም ለለውጡ የከፈሉት መስዋዕትነት አድርገው እንዲመለከቱት ጠይቀዋል።

ወጣቶቹ ዛሬ ሲለቀቁ ሰላም ለሁላችንም ስለሆነች እንጠብቃት የሚል ጽሁፍ የታተመበት ቲሸርት እንዲለብሱ መደረጋቸውን ለማወቅ ተችሏል።

ከአንድ ወር በላይ በአደገኛ ሁኔታ በጦላይ የወታደራዊ ካምፕ ታፍሰው የተወሰዱት የአዲስ አበባ ወጣቶች ዛሬ መፈታታቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።

በኮሚሽኑ መግለጫ ወጣቶቹ ህገመንግስታዊና የህግ ጉዳዮች ላይ ስልጠና ከተሰጣቸው በኋላ መለቀቃቸው ገልጿል።

ስልጠናውን በማጠናቀቅ ሰላምን እንጠብቃት የሚል መፈክር የተጻፈበት ቲሸርት እንዲለብሱ የተደረጉት የአዲስ አበባ ወጣቶች ወደ ቤተሰቦቻቸው እየመጡ መሆኑንም ፖሊስ አስታውቋል።

ቁጥራቸው ከ1170 በላይ የሆኑት ወጣቶች ባለፈው መስከረም ወር በአዲስ አበባ ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘ በጅምላ ታፍሰው የታሰሩ መሆናቸው ታውቋል።

የወጣቶቹ እስር ከፍተኛ ቁጣን የቀሰቀሰ ነበር። በአፈሳ የተከናወነው እስር የህግ ጥሰት ያለበት፣ የህገመንግስቱን መሰረታዊ መብቶች ያፈረሰ፣ ሰብዓዊ መብትን የረገጠ መሆኑን በመጥቀስ እንዲፈቱ የሚጠይቅ ዘመቻ መካሄዱም የሚታወስ ነው።

በመንግስት ባለስልጣናት የተለያዩና እርስ በእርስ የሚጋጩ መግለጫዎች የተሰጡበት የአዲስ አበባ ወጣቶች እስር ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት ድጋፍ በመስጠት ቀዳሚ ለሆነው የአዲስ አበባ ነዋሪ ቅሬታ የሚፈጥር ሆኖ ቆይቷል።

ባለፈው ሰኞ የተጀመረውና ትላንት ያበቃው የማህበራዊ ድረገጽ ዘመቻም በመንግስት ላይ ጫና መፍጠሩ የሚታወስ ነው።

ዛሬ የተለቀቁት የአዲስ አበባ ወጣቶችን በተመለከተ በምክር ቤት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ያለአግባብ የታሰሩ ከነበሩ ለለውጡ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ይቁጠሩት በማለት አልፈውታል።