ሁለት የሰብዓዊ መብትና የህግ ባለሙያዎች ፍርድ ቤት ቀረቡ

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 8/2011)የአዲስ አበባ ወጣቶችን በማደራጀት ክስ የተመሰረተባቸው ሁለት የሰብዓዊ መብትና የህግ ባለሙያዎች ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ።

ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉና ሚካዔል መላከ አዲስ አበባ ከሌላ አካባቢ በመጣ ሰው አትተዳደርም የሚል ቅስቀሳ በማድረግና የአዲስ አበባ ወጣቶችን ሲያደራጁ ነበር የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።

የፖሊስ ክስ ላይ ለዚህ እንቅስቃሴ የሚረዳ ግንኙነት ከፍልስጤም ኤምባሲ ጋር መደረጉን የሚያመለክት ነው።

የአዲስ አበባ ወጣቶችን ለማደራጀት ተንቀሳቅሰዋል የተባሉ ሌሎች ሰዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታውቋል።

ባለፈው ቅዳሜ በአዲስ አበባ ሀሮምሳ በሚል የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ የአዲስ አበባ ወጣቶችን የማደራጀት እንቅስቃሴ በይፋ መጀመሩ የሚታወስ ነው።

የህግ ባለሙያና ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሚካዔል መላከ የተያዙት ትላንት ነበር።

ጠበቃ ሄኖክ ትላንት ቢሮ ውስጥ እንዳለ በፖሊስ መያዙን የሚገልጹት የኢሳት ምንጮች በቢሮው የሚጠቀምባቸው ኮምፒውተሮችና ሌሎች እቃዎች ተበርብረው መወሰዳቸው ታውቋል።

ዛሬ የአራዳ የመጀመሪያው ፍርድ ቤት ጠበቃ ሄኖክና ሚካዔል ላይ የተከፈተውን ክስ ማዳመጡን ነው ለማወቅ የተቻለው።

በፖሊስ የቀረበው ክስ የአዲስ አበባን ወጣቶች ለማደራጀት ተንቀሳቅሳችኋል የሚል ነው።

ፖሊስ በክስ መዝገቡ ጠበቃ ሄኖክና ሚካዔል መላከ፡ አዲስ አበባን ከሌላ ክልል የመጣ ከንቲባ ሊመራት አይገባም የሚል አቋም ይዘው ሲቀሰቅሱ ነበር ሲል አመልክቷል።

በተጨማሪም የፍልስጤም ወዳጅነት ማህበር ማቋቋም የሚል የፖሊስ ክስ እንደሚገኝበትም ጉዳዩን የተከታተሉ ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።

ከፍልስጤም ኤምባሲ ጋር በመገናኘት የወዳጅነት ማህበር ለመመስረት ሲንቀሳቀሱ ደርሼባቸዋል ነው የሚለው ፖሊስ።

ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉ በተለይ በህወሃት አገዛዝ ዘመን በግፍ ለሚታሰሩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና ጋዜጠኞች በነጻ ጥብቅና በመቆም የሚታወቅ ነው።

በቅርቡም ከአዲስ አበባ ግጭት ጋር በተያያዘ ለታሰሩት የአርበኞች ግንቦት ሰባት አቀባበል ኮሚቴ አባላት ጠበቃ በመሆን ቆሞላቸዋል።

ለአሁኑ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ለሆኑትና በህወሀት አገዛዝ በተደጋጋሚ ለእስር ተዳርገው ለነበሩት ለአቶ ታዬ ደንደአም ጠበቃ በመሆን ተሟግቶላቸዋል።

በተመሳሳይ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ሚካዔል መላከም በግፍ ለሚታሰሩ ሰዎች ከፍተኛ አስተዋጽዖ በማድረግ የሚታወቅ ነው።

በትላንትናው ዕለት በፖሊስ ተይዘው ፍርድ ቤት የቀረቡት ሁለቱ ግለሶቦች የተከሰሱበት ወንጀል መሆኑን በተመለከተ የህግ ባለሙያዎች ግራ የሚያጋባ ሲሉ ገልጸውታል።

መደራጀትና ሀሳብን በነጻነት መግለጽ በህገመንግስቱ በተረጋገጠበት ሁኔታ የተከሰሱበት ጉዳይ የሚያስጠይቅ እንዳልሆነ ነው የህግ ባለሙያዎች የሚገልጹት።

ከሁለቱ ግለሰቦች በተጨማሪ ለጊዜው ቁጥራቸው ያልተገለጸ በርካታ የአዲስ አበባ ወጣቶች የመደራጀት እንቅስቃሴ እያደረጋችሁ ነው በሚል መታሰራቸውን ለማወቅ ተችሏል።

ባለፈው ቅዳሜ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆችን ለማደራጀት የተጠራው ስብሰባ መፈቀዱን የሚጠቅሱ ወገኖች መደራጀት ለአንዱ ተፈቅዶ ለሌላው ወንጀል የሚሆንበት ምክንያት ግራ የሚያጋባ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በሰብዓዊ መብት ተሟጋችና የህግ ባለሙያ ሄኖክ አክሊሉና ሚካዔል መላከ ላይ የተመሰረተውን ክስ በተመለከተ ፖሊስ ተጨማሪ ጊዜ በመጠየቁ ለሚቀጥለው ሳምንት መጨረሻ ቀጣይ ቀጠሮ መሰጠቱን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።