(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 7/2011) በደቡብ ኢትዮጵያ በጎፋና ወላይታ በወረርሽኝ 20 ሰዎች መሞታቸው ታወቀ።
በጎፋ ዳራማሎ ወረዳ በትክትክ ወረርሽኝ 10 ሰዎች ሲሞቱ በወላይታ ኦፋ ወረዳ የቢጫ ወባ በሽታ ተከስቶ በተመሳሳይ 10 ሰዎች መሞታቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በወረርሽኝ ደረጃ የተከሰቱትን እነዚህን በሽታዎች ለመቆጣጠር በመንግስት በኩል አፋጣኝ ርምጃ ካልተወሰደ የከፋ ጉዳት ሊደርስ ይችላል ተብሏል።
ትክትክ የተሰኘው በሽታ ከምድር ገጽ ላይ ጠፍቷል ከተባለ ዓመታት ተቆጥሯል። የመንግስታቱ ድርጅት የጤና ተቋም መረጃ እንደሚያመልክተውም ትክትክ በዓለም ለይ ከጠፉ በሽታዎች ተርታ የሚመደብ ነው።
ለኢሳት ከደቡብ ኢትዮጵያ ጎፋ የደረሰው መረጃ እንደሚያመልክተው ምልክቶቹ የትክትክ በሽታ የሆነ ወረርሽ ተከስቷል።
ስማቸውን መጠቀስ ያልፈለጉ የጎፋ ዞን ዳራማሎ ወረዳ አንድ የጤና ባለሙያ እንደገለጹት በወረርሽኝ መልክ የተከሰተው በሽታ ከትክትክ ጋር የሚመሳል ነው።
የዞኑ የጤና ቢሮ ሃላፊዎች ጉዳዩን በሚስጢር ይዘው ለክልል የጤና ቢሮ ሪፖርት ያደረጉ ሲሆን በመንግስት ደረጃ ይፋ በሆነ መልኩ ወረርሽኝ ስለመከሰቱ እንዳይገለጽ መደረጉን ነው ለማወቅ የተቻለው።
በዚህ ወረርሽ እስከአሁን 10 ሰዎች መሞታቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸው ቁጥር ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል ነው የጠቀሱት።
በወረዳው ባለው የመርጃ ውስኑነት የተነሳ የወረርሽኙ መጠን ማወቅ እንዳልተቻለ የተገለጸ ሲሆን በተመሳሳይ በሽታ የተጠቁ ሰዎች ወደጤና ማዕከላት በመሄድ ላይ ናቸው ተብሏል።
ጉዳዩን ለማጣራት ወደ ጎፋ ደውለውን ሊሳካልን አልቻለም።
በተመሳሳይ በወላይታ ዞን ኦፋ ወረዳ የቢጫ ወባ በሽታ መስፋፋቱን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በሽታ ወደ ወረርሽኝ የተቀየረ መሆኑን የሚገልጹት የኢሳት ምንጮች ከ10 በላይ ሰዎች በበሽታው ምክንያት ህይወታቸው ማለፉን ለማወቅ ተችሏል።
ቢጫ ወባ በአከባቢው የተለመደ ቢሆንም ሰሞኑን የተከሰተው ባለተመደ መልኩ አስደንጋጭ ነው እንደሆነ ከአከባቢው ያገኘነው መረጃ ያመልክታል።
በርካታ ሰዎች በበሽታው ተይዘው በጤና ጣቢያዎች የሚገኙ ሲሆን አስቸኳይ እርምጃ ካልተወሰደ በበሽታው ብዙ ሊያልቅ እንደሚችል የጤና ባለሙያዎችን በመጥቀስ የኢሳት ምንጮች ካደረሱን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።