በአየሁ እርሻ ልማት የሰብአዊ መብት ረገጣ እየተፈጸመ ነው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 7/2011) በአየሁ እርሻ ልማት ሰራተኛና የአካባቢው ነዋሪዎች ከፍተኛ የጉልበት ብዝበዛና የሰብአዊ መብት ረገጣ እየተፈጸመባቸው መሆኑን ገለጹ።

በኢትዮ-አግሪ ሴፍት ኩባንያ ስር ያለው የአየሁ እርሻ ልማት በአካባቢው የተፈጥሮ ሃብትና ምርት እየተጠቀመ ሰራተኞቹ ግን ለከፍተኛ ድህነትና እንግልት መዳረጋቸውን ነው የሚናገሩት።

ፋይል

የሼህ አላሙዲን ኩባንያ ነው የተባለው ኢትዮ-አግሪ ሴፍት በእርሻ ልማቱ ከ13 አመት በታች የሆኑ ሕጻናትን ጉልበትም እየበዘበዘ መሆኑም ታውቋል።

የአየሁ እርሻ ልማት በአማራ ክልል አዊ ዞን ጓጉሳ ወረዳ ውስጥ የሚገኝ አካባቢ ነው።

በእርሻ ልማቱ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ይገኛሉ።

ታዳጊ ሕጻናትና ወጣቶች ደግሞ ከ7ሺ እስከ 8ሺ የሚደርሰውን ቁጥር ይይዛሉ።

እነዚሁ ነዋሪዎች ታዲያ የሼህ አላሙዲን ኩባንያ በሆነው ኢትዮ-አግሪ ሴፍት ከፍተኛ የጉልበት ብዝበዛና የሰብአዊ መብት ረገጣ እየተፈጸመባቸው መሆኑን ይናገራሉ።

በተለይም እስከ 14 አመትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሕጻናት ላይ ሳይቀር ጉልበታቸው እየተበዘበዘ ለከፍተኛ ድህነት በመጋለጣቸው የድረሱልን ጥሪያቸውን አሰምተዋል።

የአየሁ ጉግሳ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ነጋ ስዩም 340 የሚደርሱ በአካባቢው የነበሩ ሰራተኞች በኩባንያው የደረሰባቸውን ችግር መነሻ በማድረግ ወደ ሌላ አካባቢ እንዲሰፍሩ ተደርገዋል ብለዋል።

እናም በአየሁ እርሻ ልማት እየተፈጸመ ያለው የሕጻናት የጉልበት ብዝበዛና የሰብአዊ መብት ጥሰት ከአቅማችን በላይ ሆኖብናል ነው ያሉት።

በአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ/አዴፓ/የአዊ ዞን ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጥላሁን ወርቅነህ በበኩላቸው የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ የተቀጣሪዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች ጥቅማቸው የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ የተቀጣሪዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች ጥቅማቸው እንዲጠበቅ ቢደነግግም በአየሁ እርሻ ልማት የሚፈጸመው ግፍ ግን አሰቃቂ ነው ብለዋል።

የኢትዮ አግሪ ሴፍት የአስተባባሪና የሰው ሃይል ስራአስኪያጅ አቶ ሚሊዮን ከበደ ስለጉዳዩ ለኢሳት እንደገለጹት ከ14 ዓመት በላይ የሆኑ ታዳጊዎችን ማሰራት በፖሊሲያችን ባይፈቀድም ችግር ስላለባቸው በወላጆች ጥያቄ እናሰራለን ሲሉ ችግሩን አምነዋል።

በአጠቃላይ በአካባቢው ነዋሪዎች የሚደርሰው ችግር ግን በህገወጥ በሰፈሩትና ጡረታ ወጥተው ከድርጅቱ በተሰናበቱ ላይ ስለሆነ እኛም ክልሉም የአካባቢው አስተዳደርም በጋራ የምንፈታው ይሆናል ነው ያሉት።

የአየሁ እርሻ ልማት በመንግስት ሲተዳደር ቆይቶ በ1993 ለሼህ አላሙዲን ተላልፎ እና ሰብል በማምረት ከፍተኛ ትርፍ በሚያካብተው ኢትዮ አግሪ ሴፍት እየተዳደረ ያለው።

ኩባንያው 6 መቶ ቋሚ ሰራተኞች ሲኖሩት ከ4ሺህ እስከ 5ሺህ የሚደርሱት ግን ጊዜያዊ ናቸው።

በአከባቢው ያሉት የአየሁ እርሻ ልማት ነዋሪዎች በኩባንያው ተጽዕኖ ምክንያት ቤት መስራት፣ ማደስና እርሻ ማረስ እንደማይችሉ ለመገንዘብ ችለናል።

እናም የአካባቢው ሕዝብ በከፍተኛ ድህነት ውስጥ ይገኛል።