አቶ ተመስገን ጥሩነህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት ጉዳዮች አማካሪ ሆኑ

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 7/2011)አቶ ተመስገን ጥሩነህ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የብሔራዊ ደህንነት ጉዳዮች አማካሪ ሆነው ተሾሙ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሌሎች ተጨማሪ ሶስት ግለሰቦችም ሹመት ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ሲወጡ የብሔራዊ ደህንነት ጉዳዮች አማካሪ ሆነው የተሾሙት አቶ አባዱላ ገመዳ በአጭር ጊዜ ውስጥ በጡረታ ከተሰናበቱ ወዲህ ስፍራው ሰው ሳይሾምበት ቆይቷል።

አሁን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት ጉዳዮች አማካሪ ሆነው የተሾሙት አቶ ተመስገን ጥሩነህ በኢንሳ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ባልደረባ የነበሩ የብአዴን አባል መሆናቸው ተመልክቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በሰጡት ሹመት ከብሔራዊ ደህንነት አማካሪው አቶ ተመስገን ጥሩነህ በተጨማሪ የቀድሞው የደቡብ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ደሴ ዳልኬ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የግብርናና መስኖ አማካሪ ሲሆኑ የአማራ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ብናልፍ አንዱአለም የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ዋና አስተባባሪ ሆነው ተሹመዋል።

ይህ ስፍራ በሕወሃቷ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር ተይዞ የነበረ ነው።

ትላንት ከሚኒስትርነታቸው የለቀቁት አቶ መለስ አለሙ የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ማስተባባሪ ምክትል ሃላፊ ሆነው ተሹመዋል።

አዲሶቹ ተሿሚዎች አራቱም ስልጣናቸው በሚኒስትር ማዕረግ እንደሆነም ተመልክቷል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት ጉዳዮች አማካሪ ሆነው የተሾሙት አቶ ተመስገን ጥሩነህ በቅርቡ የኢንሳ ዳይሬክተርነትን ከሕወሃቱ ሜጀር ጄኔራል ተክለብርሃን ወልደአረጋይ ተረክበው እንደነበር ይታወሳል።

እሳቸውን ተክቶ ለኢንሳ ዳይሬክተርነት ማን እንደተሾመ የታወቀ ነገር የለም።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት ጉዳዮች አማካሪነት ስፍራ በአቶ መለስ ዜናዊ የስልጣን ዘመን በአቶ ሙሉጌታ አለምሰገድ፣በአቶ ጸጋዬ በርሔ በአጠቃላይ የሕወሃት ሰዎች በቋሚነት ተይዞ የቆየ ሲሆን በአቶ ሃይለማርያም የስልጣን ዘመንም ስፍራው በሕወሃት ሰዎች እጅ መቆየቱ ይታወሳል።