ቱርክ በአገሯ ያለውን የሳውዲን ኢምባሲ መረመረች
( ኢሳት ዜና ጥቅምት 06 ቀን 2011 ዓ/ም ) በሳውዳረቢያዊው ዜጋ ጋዜጠኛ ጀማል ካሾጊ ግድያ ዙሪያ የሚደረገውን ምርመራ አጠናክራ የቀጠለችው ቱርክ በአገሯ ባለው የሳውዲ ኢምባሲ በመግባት ምርመራ ማካሄዷ ታውቋል። ኢስታንቡል የሚገኘው ቆንስላ ተወካይ የሆኑት ሙሃመድ አል ኦታይቢ በግል አውሮፕላን ከአገሪቱ መውጣታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
በሳውዲ ንጉሳዊ ቤተሰብ ላይ ከፍተኛ ትችት በማቅረብ የሚታወቀው ጋዜጠኛ ካሾጊ፣ ከቀድሞ ባለቤቱ ጋር የነበረውን ፍቺ ለማጠናቀቅ እና አዲሷን እጮኛውን ለማግባት ወደ ቆንስላው ጽ/ቤት ካመራ በሁዋላ፣ የት እንደገባ አልታወቀም። ቱርክ ፣ በእለቱ ወደ አገሯ የገቡ 15 የሳውዲ የደህነት ሰራተኞች ቆንስላው ውስጥ ግድያ እንደፈጸሙ እየገለጸች ሲሆን፣ ሳውድ አረቢያ ግን ታስተባብላለች። የቆንስላ ጽ/ቤቷ እንዳይፈተሽ ስታንገራግር የቆየችው ሳውድ አረቢያ በመጨረሻ ጽ/ቤቷን ለፍተሻ ክፍት አድርጋለች። አሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯን ማይክ ፖፒዮን ወደ ሳውድአረቢያ ልካለች።
የዋሽንግተን ፖስት ዘጋቢ የሆነውን ካሾጊ ግድያን ተከትሎ በሳውድ አረቢያ ላይ የሚደርሰው አለማቀፍ ጫና በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።