በአማሮ ወረዳ 3 የ መከላከያ ሰራዊት አባላት በታጣቂዎች ተገደሉ

በአማሮ ወረዳ 3 የ መከላከያ ሰራዊት አባላት በታጣቂዎች ተገደሉ
( ኢሳት ዜና ጥቅምት 05 ቀን 2011 ዓ/ም ) የአካባቢው ነዋሪዎች በሰራዊቱ አባላት ላይ ጥቃት የፈጸሙት የኦነግ ታጣቂዎች ናቸው ቢሉም፣ በመንግስት በኩል እስካሁን የተሰጠ ማስተባበያም ሆነ ማረጋገጫ የለም።
የግድያው መንስዔ ላለፉት 16 ወራት የዘለቀው በአማሮ ወረዳ የሚካሄደው በጉጂና በኮሬ ማህበረሰቦች መካከል ያለው ግጭት እንደገና በማገርሸቱ ነው። ባለፈው አርብ በስራ ላይ በነበሩ የኮሬ ተወላጆች ላይ በተፈጸመ ጥቃት አንድ የ10 አመት ታዳጊ ወጣት ሲገደል 2 ሌሎች አርሶአደሮች ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ ቆስለዋል። ግጭቱ በዳኖ ቀበሌም ቀጥሎ በኮሬ በኩል አቶ ጌዲዮን ሊባ እና ኢለሙሳ አየለ የተባሉት ግለሰቦች የቆሰሉ ሲሆን፣ ግጭቱን ለማብረድ ጣልቃ በገቡት የመከላከያ አባላት ላይ በደረሰ ጥቃት 2 የመከላከያ ሰራዊት አባላት ወዲያውኑ ሲገደሉ፣ አንደኛው ደግሞ ቆስሎ በህክምና ላይ እያለ ህይወተሩ አልፏል። ሌላ አንድ ወታደርም በከባድ ሁኔታ ቆስሎ ሆስፒታል ተኝቷል። የመከላከያ ሰራዊት በወሰዱት የአጸፋ እርምጃ ሁለት የታጠቁ ሃይሎች መገደላቸውን የአይን እማኞች ገልጸዋል። የመከላከያ አባላቱ የቀብር ስነስርዓት ዛሬ ተፈጽሟል።
በቡርጂና ጉጂ ብሄረሰቦች መሃል በተደረገው የተኩስ ልውውጥም እንዲሁ በቡርጂ በኩል አንድ አርሶ አደር በከፍተኛ ሁኔታ ቆስሏል።
ከአማሮ ዲላ፣ ከቡርጂ ሃገረማርያም የሚወስዱ መንገዶች ለአመት ከአራት ወር ያክል በመዘጋታቸዉ የሁለቱም ወረዳ ህዝቦች በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰቃዩ ነው።
የመከላከያ ኢታማዦር ሹሙ ጄ/ል ሳዕረ መኮንን ሰራዊታቸው በአካባቢው ተሰማርቶ ጸጥታ እያስከበረ እንደሚገኝና ይህ ሰራዊት ወደ ቡራዩ፣ አዲስ አበባና በሶሚሊ እና ኦሮምያ ድንበሮች አካባቢ ተልዕኮ ግዳጁን ሲወጣ እንደነበር ገልጸዋል።