(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 1/2011)ከድሬደዋ ወደ ቢሾፍቱ ከአንድ ወር በፊት ሲበር የተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር ሃይል አውሮፕላን የምርመራ ውጤት ይፋ ተደረገ።
የኢትዮጵያ አየር ሃይል አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት አውሮፕላን ምንም የቴክኒክ ችግር እንዳልገጠመው በምርመራ ተረጋግጧል።
ነሐሴ 24/2010 ከረፋዱ 3 ሰአት ከ40 ደቂቃ ከድሬደዋ መነሳቱ የተገለጸው የበረራ ቁጥር 808 ዳሽ 6 አውሮፕላን፣ኤጀሬ በተባለ ከተማ አቅራቢያ መከስከሱ ይታወሳል።
አብራሪዎቹንና የቴክኒክ ባለሙያዎቹን ጨምሮ 17 ሰዎች ያለቁበትን ይህንን አደጋ ሲመረምር የቆየው 5 አባላት ያሉት የምርመራ ቡድን አደጋው በቴክኒክ ችግር አለመፈጠሩን ይልቁንም በመጥፎ አየር ሳቢያ የተፈጠረ መሆኑን ገልጿል።
የኢትዮጵያ አየር ሃይል አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ይልማ መርዳሳ የምርመራ ውጤቱን በተመለከተ ለመከላከያ ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ በ8 ሺ 500 ጫማ ላይ ሲበር የነበረውን አውሮፕላን ወደ 7 ሺ 500 ሲወርድ በገጠመው ደመና ሳቢያ ኤጀሬ ከተማ አቅራቢያ ከሚገኝ ተራራ ጋር በመጋጨቱ አደጋው ተከስቷል።
ከደመና በታች ለመውረድ ሲሞክር ከተራራ ጋር ተጋጭቶ በተከሰከሰው አውሮፕላን አብራሪዎቹን ጨምሮ በአጠቃላይ 17 ሰዎች አልቀዋል።
የአየር ሃይል አባላትና ቤተሰቦቻቸውም ከሰለባዎቹ ውስጥ መሆናቸው ተመልክቷል።