ኦነግ ትጥቅ አልፈታም ማለቱ ተገቢ አይደለም ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 1/2011)የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር ሊቀመነበር አቶ ሌንጮ ለታ ኦነግ ትጥቅ አልፈታም ማለቱ ተገቢ አይደለም አሉ።

ወጣቱ በባዶ እጁ ታንክ ፊት በሚጋፈጥበት ጊዜ የኦነግ ሰራዊት የት ነበር ሲሉ አቶ ሌንጮ ለታ በሀገር ውስጥ ከሚሰራጨው አሀዱ ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ ገልጸዋል።

ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት ከፈለግን በሀገር ውስጥ መኖር ያለበት ሰራዊት የመንግስት ብቻ መሆን አለበት ያሉት አቶ ሌንጮ ለታ የኦነጉ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ የተናገሩት ግራ የሚያጋባ ነው ብለዋል።

የኦነግ ሰራዊት የት ነበር? በማን ነው የሚታዘዘው? የሚሉ ጥያቄዎችን ያነሱት አቶ ሌንጮ ለታ ሰራዊቱ አለ ከተባለም ትጥቅ አልፈታም ማለት አይችልም ሲሉ አቋማቸውን አንጸባርቀዋል።

ኦነግ ትጥቅ አልፈታም የሚለው ማንን ለመውጋት ነው ሲሉ ይጠይቃሉ አቶ ሌንጮ ለታ።