ታዋቂው የነጻነት ታጋይ ኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህ መታመማቸው ታወቀ
( ኢሳት ዜና መስከረም 03 ቀን 2011 ዓ/ም ) በኢትዮጵያ የቀድሞው ሰራዊት ውስጥ በአየር ሃይል ምድብ ከፍተኛ ወታደራዊ ጀብዱ በመፈጸም የተለያዩ የጀግና ሜዳሊያዎችን የተሸለሙት የቀድሞው የአርበኞች ግንባር መሪ ኮ/ል ታደሰ ሙሉነህ ታመው ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ነው። ኮ/ል ታደሰ አስመራ ውስጥ ኦሮታ ሪፈራል ሆስፒታል ተኝተው ህክምና እየተከታተሉ ሲሆን፣ ወደ ኢትዮጵያ በፍጥነት ሄደው ለመታከም ዝግጅት መጀመራቸውም ታውቋል።
የኤርትራ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ኮሎኔል ታደሰ በፍጥነት ወደ አገራቸው ገብተው አስፈላጊውን ህከልምና እንዲከታተሉ የታጋዩ ደጋፊዎች እና ቤተሰቦች ተማጽኖዋቸውን አቅርበዋል። በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የተጀመረውን ግንኙነት ተከትሎ የተቃዋሚ ድርጅቶችና የሁለቱ አገራት ዜጎች በነጻነት መንቀሳቀስ መጀመራቸውን ተከትሎ ፣ ኮ/ል ታደሰም ይህን አገጣሚ ተጠቅመው ወደ አገራቸው እንዲመለሱና ተገቢው ክብር እንዲሰጣቸው የኢትዮጵያ መንግስትም አስፈላጊውን ጥረት እንዲያደርግ ደጋፊዎቻቸው ጥሪ አቅርበዋል።
ኮ/ል ታደሰ የአርበኞች ግንባርን በበላይነት ሲመሩ ቆይተው በድርጅቱ ውስጥ በተፈጠረ መከፋፈል ከፖለቲካው ራሳቸውን አግልለው ቆይተዋል። ኤርትራ ውስጥ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ታስረው በቅርቡ የተፈቱት ኮ/ል ታደሰ፣ ብዙም ሳይቆዩ የሰውነት ክብደታቸው በመቀነሱና እግሮቻቸው ማበጥ በመጀመሩ ወደ ሆስፒታል ማምራታቸውንና በአሁኑ ሰዓትም ህክምና እየተከታተሉ እንደሚገኙ ታውቋል።
ኮ/ል ታደሰ ሶማሊ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ከፍተኛ ጀብዱ ከፈጸሙ የአየር ሃይል አብራሪዎች መካከል አንዱ ናቸው።