የረጲ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በተመረቀ በሁለት ሳምንቱ ስራ አቆመ

የረጲ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በተመረቀ በሁለት ሳምንቱ ስራ አቆመ
( ኢሳት ዜና መስከረም 03 ቀን 2011 ዓ/ም ) በአዲስ አበባ ከተማ 2.6 ቢሊዮን ብር ወጪ ወጥቶበት የተገነባው የረጲ ደረቅ ቆሻሻ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ነሐሴ 13 ቀን 2010 ዓ.ም. ቢመረቅም በሁለት ሳምንቱ ስራውን አቋርጧል።
ለፕሮጀክቱ አገልግሎት መቋረጥ ያልተጠናቀቁ ሥራዎች መኖራቸውን በምክንያትነት ቢጠቀስም፣ የካምብሪጅ ኢንዱስትሪስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ዓለማየሁ ግን ”የእኛ ኃላፊነት ፕሮጀክቱን አጠናቆ የአራት ቀናት ሙከራ ማድረግ እንጂ፣ ሥራውን ማስቀጠል ኃላፊነታችን አይደለም” ማለታቸውን ሪፖርተር ዘግቧል፡፡
በኃይል ማመንጫው ያደረጉትን የመጀመርያ ሙከራ በመንግሥት እንዲደገም መጠየቁን የተናገሩት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፣ በውላቸው መሠረት ሙከራውን ሊደግሙትም ላይደግሙትም እንደሚችሉ አስታውቀዋል፡፡
የረጲ ደረቅ ቆሻሻ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የኮንትራት ውሉ በተፈረመበት ወቅት 50 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያመነጭ ነበር። ነገር ግን በግንባታው ምረቃው ወቅት የማምረት አቅሙ በግማሽ ቀንሶ 25 ሜጋ ዋት ብቻ እንዲያመነጭ መደረጉን እና በካምብሪጅ ኢንዱስትሪስ ኩባንያ፣እና ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መካከል ውዝግብ መፈጠሩን ኢሳት መዘገቡ ይታወሳል።
በዶ/ር ደብረጺዮን ትዕዛዝ ስራው ከ5 አመት በፊት ለተባለ ኩባንያ ያለግልጽ ጫረታ ተሰጥቷል። ወጪው ሙሉ በሙሉ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብድር የተሸፈነ ነው።
ኬምብሪጅ እንዱስትሪስ ሊሚትድ በብሪቲሽ ቨርጂን አይላንድስ እንደተመዘገበ በውል ስምምነቱ ላይ ሰፍሮ የሚገኝ ቢሆንም፣ የኩባንያው የአክሲዮን ባለቤቶች የኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እንደሆኑ ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች ማስታወቃቸውን ኢሳት መዘገቡ ይታቀሳል።
ኬምብሪጅ በኮንትራት ስምምነቱ መሰረት ማሟላት ያለበትን ነገር ሳያሟላ ፕሮጀክቱን ለማስረከብ ፍላጎት ያለው ቢሆንም፣ የመብራት ሃይል ሰራተኞች ፕሮጀክቱን ለመረከብ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።