(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 28 /2010) በኢትዮጵያ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣዎች የስራ ማቆም አድማን ሲመሩ የነበሩ 9 ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ።
ግለሰቦቹ አለምአቀፍ የበረራ ሂደትን ለማስተጓጎል በተለይም ከውጭ ሀገራት የሚመጡ አውሮፕላኖች እንዳያርፉ ጥረት ሲያደርጉ ተገኝተዋል በሚል ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት ተብሏል።
በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ሰራተኞች ዘንድ ሲደረግ የቆየውን የስራ ማቆም አድማ አስተባብረዋል እንዲሁም መርተዋል ተብለው 9 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል ተኮላ ግለሰቦቹ የተያዙት በፍርድ ቤት ማዘዣ ወጥቶባቸው ነው ብለዋል። በአሁኑ ወቅትም ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛል ነው ያሉት።
ግለሰቦቹ የታሰሩት አለምአቀፍ የበረራ ሂደትን ለማስተጓጎል በተለይም ከውጭ ሀገራት የሚመጡ አውሮፕላኖች እንዳያርፉ ጥረት ሲያደርጉ ነበር በሚል ነው።
የስራ ማቆም አድማ ማድረግ የዜጎች መብት ቢሆንም ሰራተኞቹ ለምን እንደታሰሩ ፖሊስ ማብራሪያ አልሰጠም።
በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ሰራተኞች የመብት ጥያቄ ስላነሱ መታሰራቸው ሕገመንግስታዊ መብታቸውን የሚጻረር ነው የሚሉ ወገኖች አሉ።
ሰራተኞቹ ያነሱት የመብት ጥያቀ ትክክል ባይሆን እንኳ ከስራ ማባረርና ደሞዝ መቅጣት እየተቻለ ለምን መንግስት የእስር ርምጃ እንደወሰደ ግልጽ እንዳልነላቸውም የተለያዩ ወገኖች በመግለጽ ላይ ናቸው።