(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ24/2010)በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ሉሜ ወረዳ ከተከሰከሰው የአየር ሃይል የመጓጓዣ አውሮፕላን ውስጥ ከሞቱት 18 ሰዎች መካከል ሲቪሎች ተሳፍረው መገኘታቸው ያልተለመደ መሆኑን የቀድሞው አብራሪ ካፒቴን ተሾመ ተንኮሉ ገለጹ።
ከሟቾቹም መካከል 15ቱ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ሲሆኑ ሶስቱ ደግሞ ሲቪሎች መሆናቸው ታውቋል።–ከሟቾቹ መካከል ሁለት ሴቶችና ሁለት ልጆች መኖራቸውን መረጃዎች አመልክተዋል።
የአደጋው መንስኤም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ካፒቴኑ ገልጸዋል።
የአደጋው መንስኤ እስካሁን ያልታወቀና በመጣራት ላይ መሆኑ ቢገለጽም ባለሙያዎቹ ግን ምርመራው አዳጋች ነው ይላሉ።
የቀድሞ የአየር ሃይል አብራሪና የበረራ መምህር የነበሩት ካፒቴን ተሾመ ተንኮሉ አካባቢውን በደንብ እንደሚያውቁትና ብዙ ጊዜም የአየር ንብረቱ አስቸጋሪ እንደሆነ አብራርተዋል።
ካፒቴን ተሾመ የተከሰከሰው የአየር ሃይል መጓጓዣ አውሮፕላን ካናዳ ስሪትና ዳሽ ሲክስ የሚል መለያ እንዳለውም ተናግረዋል።
አየር ሃይሉ ለመጓጓዣነት የጠቀምበታል የተባለው አውሮፕላን ከድሬደዋ ወደ ቢሾፍቱ በመብረር ላይ እያለ ነው የመከስከስ አደጋው የገጠመው።
ለዚህ ምክንያት አድርገው የሚያስቀምጡት ደግሞ በሃገር ውስጥ እንዲህ አይነቱ አደጋ ሲከሰት ምርመራ የሚያደርግ ባለሙያ አለመኖሩ ነው።