በጎንደር ለአርበኞች ግንቦት ሰባት አቀባበል ዝግጅት እየተደረገ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 24/2010) በጎንደር ለአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ አመራሮችና አባላት አቀባበል ለማድረግ የተቋቋመው ኮሚቴ ዝግጅት እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ።

ዘመቻ ነጻ ትውልድ በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው የአቀባበል ፕሮግራም በቅርቡ ከእስር የተፈታችው ታጋይ ወይዘሮ እማዋይሽ  ዓለሙ በተገኙበት ዛሬ በጎንደር ስብሰባ ማካሄዱ ታውቋል።

በሌላ በኩል በአዲስ አበባ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ አመራሮችንና አባላቱን ለመቀበል በየክፍለ ከተማው ዝግጅቱ ተጠናክሮ እየተካሄደ መሆኑን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

የአርበኞች ግንቦት ሰባት የጎንደር አቀባበል ኮሚቴ በዛሬው ዕለት በጎንደር ፋሲል ግምብ ስብሰባ አካሂዷል።

የንቅናቄው አመራሮችንና አባላትን ለመቀበል ዝግጅት ሲያደርግ የቆየው ኮሚቴው ቀሪ ስራዎችን በማጠናቀቅ ዕለቱን እየተጠባበቁ መሆናቸውን ነው የኮሚቴው አባላት ለኢሳት የገለጹት።

ኮሚቴው በቀጣይ ህብረተሰቡን በማስተባበር አቀባበሉን ደማቅ ለማድረግ የተለያዩ ክንውኖችን ተፈጻሚ ሊያደርግ መሆኑን አስታውቋል።

የአቀባበል መርሃ ግብሩን ዘመቻ ነጻ ትውልድ በሚል እንዲጠራ መደረጉን የገለጹት የኮሚቴው አባላት በትግል ወቅት የንቅናቄው አርበኞች የሚጠሩበት ስያሜን ለማስታወስ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ዛሬ በፋሲል ግምብ በተካሄደው ስነስርዓት በቅርቡ ከእስር የተፈታችው ወ/ሮ እማዋይሽ ዓለሙ በመገኘት የአቀባበል ፕሮግራሙን ህብረተሰቡ እንዲሳተፍበት ጥሪ አድርጋለች።

ወ/ሮ እማዋይሽ የጎንደር ህዝብ ውለታ በታሪክ  የሚታወስ ታላቅ ተጋድሎ የፈጸመ ነው በማለት የምስጋና መልዕክት አስተላልፈዋል።

እንግዶቻችንን እጅ ለእጅ ተያይዘን እንቀበላቸው ሲሉም ጥሪ አድርገዋል።

ወ/ሮ እማዋይሽ ዓለሙ የፊታችን ቅዳሜ አዲስ አበባ የሚገባውን አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነን በደመቀ ሁኔታ ለመቀበል መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።

በጎንደሩ የአቀባበል ኮሚቴ ውስጥ ለነጻነት ትግሉ ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈሉና በእስር ስቃይ የደረሰባቸው አንጋው ተገኝ፣ አግባው ሰጠኝ እና አለሙ ወረታው ይገኙበታል።

በሌላ በኩል በአዲስ አበባ በተለያዩ ክፍለከተሞች የተዋቀረው የአቀባበል ኮሚቴ ዝግጅቱን አጠናክሮ መቀጠሉን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

የቦሌ፡ ኮልፌ ቀራኒዮ የካ፡ አዲስ ከተማ፡ ልደታ፡ ጉለሌ፡ ጨርቆስና ሌሎች አከባቢዎች አርበኞች ግንቦት ሰባትን ለመቀበል መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በፈረንሳይ ለጋሲዮን አከባቢ ከወዲሁ በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ያሸበረቀ ዝግጅቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን ለማወቅ ተችሏል።