አብዲ ዒሌ የጠየቁት ዋስትና ውድቅ ሆነ

(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 24/2010) በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ መሀመድ ዑመር አብዲ ዒሌ የጠየቁት ዋስትና ውድቅ መደረጉ ተገለጸ።

ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ  ፍርድ ቤቱ ፈቅዷል።

ከአቶ አብዲ ዒሌ ጋር በቁጥጥር ስር የዋሉት ሌሎች የቀድሞ የሶማሌ ክልል አመራሮችም ዛሬ ፍርድ ቤት መቅረባቸው ታውቋል።

በስም መመሳሰል ታስረው የነበሩት አንድ አመራርም መለቀቃቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

አቶ አብዲ ዒሌ ትላንት በነበራቸው የፍርድ ቤት ውሎ የጤና ችግር ገጥሞኛል በሚል ውጭ ሆነው ጉዳያቸውን ለመከታተል የዋስትና መብት መጠየቃቸው ይታወሳል።

የልደታው ከፍተኛ  ፍርድ ቤት የሶማሌ ክልል የቀድሞው ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር አብዲ ዒሌ ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ አድርጎታል።

19ኛ የወንጀል ችሎት በዛሬው ውሎው አቶ አብዲ ዒሌና ሁለት ሌሎች የቀድሞ የክልሉ አመራሮችን የዋስትና መብት ውድቅ በማድረግ ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀን ተጨማሪ ጊዜ መፍቀዱን ነው ያገኘነው መረጃ የሚያመለክተው።

ትላንት በነበረው ችሎት አቶ አብዲ ዒሌ የጤና ችግር እንደገጠማቸው ጠቅሰው ውጪ ሆነው ጉዳያቸውን ለመከታተል የዋስትና መብት ጠይቀው ነበር።

በተጨማሪም በእስር ቤት የሚቀርብላቸው ምግብን በተመለከተ ቅሬታቸውን በመግለጽ ፍርድ ቤቱ እንዲመለከተው መጠየቃቸው የሚታወስ ነው።

ጉዳዩን ለዛሬ ለመመልከት የቀጠረው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዋስትናውን መብት በመከልከል በምግብ አቅርቦት በኩል ያነሱትን ጥያቄ ፖሊስ ምላሽ እንዲሰጥ አድርጓል።

ፖሊስም የሚቀርበላቸው ምግብ አግባብነት ያለው ነው ሲል ምላሽ ሰጥቷል። ከምግብ አቅርቦት በተጨማሪ የህክምና ክትትልም በተገቢው ሁኔታ እየተደረገላቸው ነው በማለት ለፍርድ ቤት አስታውቋል።

በሁለቱ ወገኖች የቀረበውን መከራከሪያ የተከታተለው ችሎቱ የዋስትና መብትኑን ውድቅ ካደረገ በኋላ ፖሊስ የምርመራ ውጤቱ ለመስማት ለመስከረም 4 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በሌላ በኩል የሶማሌ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት ፈርሃን ጣሂር ለህግ መቅረባቸው ተገለጸ።

በሶማሌ ክልል በተፈጸሙት ወንጀሎች በተለይም በቅርብ ጊዜው የጂጂጋ ግጭት ላይ እጃቸው አለበት በሚል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት ፈርሃን ጣሂር በዛሬው ዕለት ፍርድ ቤት መቅረባቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

የፖሊስ ኮሚሽነሩ ሄጎ በሚል በአቶ አብዲ ዒሌ የተደራጀውን የወጣት ሃይል መሳሪያ በማስታጠቅ ለበርካታ ሰዎች ሞትና የአካል መጉደል እንዲሁም የንብረት ውድመት ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚችሉ ነው የተመለከተው።

አቶ ጣሂር በከባድ ወንጀል ተጠርጣሪ በመሆናቸው ፖሊስ የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ጠይቆባቸው መፈቀዱም ታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም ከአቶ አብዲ ዒሌ ጋር ተባባሪ ናቸው ተብለው ታስረው የነበሩት የቀድሞ የክልሉ የመስኖ ቢሮ ሃላፊ  አቶ ሱልጣን መሐመድ መለቀቃቸው ተገለጸ።

ኃላፊው የታሰሩት በስም መመሳሰል መሆኑን የገለጸው ፖሊስ በዛሬው ዕለት ከእስር እንዲለቀቁ ማድረጉን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።