(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 21/2010) ባለፈው ቅዳሜ ከዚህ አለም በሞት የተለዩት የአሪዞናው ሴናተር ጆን ማኬይ በቀብር ስነስርአታቸው ላይ የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንዳይገኙ መናዘዛቸው ተሰማ።
ጆን ማኬይ በቀብር ስነስርአታቸው ላይ እንዲገኙ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማና ጆርጅ ደብሊው ቡሽ እንዲገኙላቸው በክብር ጋብዘዋል።
ነገር ግን ፕሬዝዳንት ትራምፕ በቀብር ስነስርአቴ ላይ እንዲገኙ አልፈግም ሲሉ ማኬይ እቺን ምድር ከመሰናበታቸው በፊት መናዘዛቸውን ሲ ኤን ኤን በዘገባው አስፍሯል።
በባራክ ኦባማ የተነደፈውን አቅምን ያማከለ የጤና ኢንሹራንስ ለማስቀረት በፕሬዝዳንት ትረምፕ በቀረበው ረቂቅ ላይ ማኬይን ህክምናቸውን ከሚከታተሉበት ሆስፒታል በመምጣት የተቃውሞ ድምጻቸውን በማሰማት የትራምፕን ሃሳብ ውድቅ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ሁለት ጊዜ ለፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ፉክክር ደርሰው በጆርጅ ደብሊው ቡሽ እና በባራክ ኦባማ የተረቱት የሪፐብሊካኑ ማኬይን በጭንቅላት ካንሰር ሲሰቃዩ ቆይተው በ81 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት የተለዩት ባለፈው ቅዳሜ ነበር።