በጅግጅጋና በሌሎችም የሶማሊ ክልሎች የሚገኙ ዜጎች አሁንም የድረሱንል ጥሪ እያሰሙ ነው

በጅግጅጋና በሌሎችም የሶማሊ ክልሎች የሚገኙ ዜጎች አሁንም የድረሱንል ጥሪ እያሰሙ ነው
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 02 ቀን 2010 ዓ/ም ) በጅግጅጋ በሚካኤል ቤተክርስቲያን ተጠልለው የሚገኙ፣ በደገሃቡር በፖሊስ ጽ/ቤት እንዲሁም በቀብሪደሃር በመከላከያ ካምፕ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች አሁንም የድረሱን ጥሪ እያሰሙ ነው።
በጅግጅጋ አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን ነዋሪዎች ቢናገሩም፣ የምግብና የውሃ ችግር አሁንም ከፍተኛ ችግር ሆኖባቸዋል። በደጋሃቡር ደግሞ የመከላከያ ሰራዊት ባለመግባቱ የክልሉ ልዩ ሃይል አባላት እርምጃ እንወስዳለን በማለት ህዝቡን እያስፈራሩት ይገኛሉ።
በቀብሪ ደሃር በመከላከያ ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ዜጎች፣ መከላከያ ወደ ስፍራው ቢገባም፣ በምግብና በመጠጥ ውሃ እየተቸገሩ መሆኑን፣ መንገዶችም በመዘጋጋታቸው ለመውጣት አለመቻላቸውን ተናግረዋል።
የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ሞቱማ መቃሳ መከላከያ ሰራዊት በጂግጂጋና በሌሎች የሶማሌ ክልል ከተሞች መግባቱን ተናግረዋል። አካባቢው በመከላከያ ስር በመሆኑ ዳግም ግጭት እንደማይነሳ ባለስልጣኑ ተናግረዋል።