የምስራቅ እዝ ወታደራዊ ፖሊስ አዛዥ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገደሉ

የምስራቅ እዝ ወታደራዊ ፖሊስ አዛዥ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገደሉ
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 02 ቀን 2010 ዓ/ም ) ኮሎኔል ጉዕሽ ከባቢሌ ወደ ሃረር ሲጓዙ ዳካታ በሚባል ቦታ ላይ ሃምሌ 28 ቀን 2010 ዓም ባልታወቁ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸው ታውቋል። አዛዡ ወደ ባቢሌ ብቻቸውን ተጉዘው እንደነበር የሚገለጹት ምንጮች፣ ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች ከመኪናቸው አውርደው ገድለዋቸዋል። አስከሬናቸው ሃምሌ 29 ቀን 2010 በምስራቅ እዝ አባላት አሸኛኘት ከተደረገለት በሁዋላ ወደ ቤተሰባቸው ተልኳል።
ኮሎኔል ጉዕሽ ከበረሃ ጀምሮ አብሮ ሲታገል የነበረና በመከላከያ ውስጥ ከፍተኛ ስልጣን የነበራቸው ሰው ናቸው። ኮሎኔሉ ሃረር ከተማ በሚገኘው ወታደራዊ ማረሚያ ቤት ውስጥ ለብዙ የመብት ታጋዮች ስቃይና ሞት ተጠያቂ እንደነበሩ ምንጮች አክለው ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በተመሳሳይ ቀን በፊቅና በባቢሌ መካከል በሚገኝ ደራራ በሚባል ከተማ ላይ አንድ የቀይ መስቀል ሰራተኛ በአሰቃቂ ሁኔታ መገደሉን ወኪላችን ዘግቧል። ሹፌሩ ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሞበት ሆስፒታል ውስጥ ይገኛል። ግድያውን የሶማሊ ልዩ ሃይሎች አባላት ፈጽመውታል ተብሎ እንደሚታመን ወኪላችን ገልጿል።
የሶማሊ ክልል ልዩ ሃይሎች ባደረሱት ጥቃት የተነሳ ከፊቅ የተፈናቀሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ትናንት ወደ ሃረር ገብተዋል። አብዛኞቹ በቻይና የመንገድ ስራ ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ናቸው። ቄሮዎች ተፈናቅለው ለመጡት ዜጎች ምግብና አልባሳት አቅርበዋል። እስከ 500 የሚሆኑ ዜጎች ዛሬ ጠዋት ወደ መሃል አገር ተሸኝተዋል።