በጅጅጋ ዜጎች በምግብና ውሃ እጦት እየተሰቃዩ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 2/2010) በጂጂጋ በቤተክርስቲያን የተጠለሉ ዜጎች በምግብና ውሃ እጦት እየተሰቃዩ መሆናቸው ተገለጸ።

ምግብ ጭነው ወደ ጂጂጋ ሲያመሩ የነበሩ ተሽከርካሪዎች መንገድ ላይ በመታገታቸው ችግሩ የከፋ መሆኑን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

በአስቸኳይ የምግብና ውሃ አቅርቦት ካልተደረገ ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ ሊፈጠር እንደሚችልም እየተነገረ ነው።

ከጂጂጋ ውጭ በአንዳንድ አካባቢዎች አለመረጋጋት እንዳለ ለማወቅ ተችሏል።

በደገሃቡር የመከላከያ ሰራዊት ባለመግባቱ ስጋት እንዳደረባቸው ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል።

ጂጂጋ ከባለፉት ቀናት አንጻር ዛሬ መረጋጋት ይታይባታል። የመከላከያ ሰራዊቱ ከተማዋን መቆጣጠሩን ተከትሎ ዝርፊያውና ግድያው ጋብ ያለ መሆኑንም መረጃዎች ያመለክታሉ።

ይሁንና አልፎ አልፎ የሚይታይ ግጭት በመኖሩ ስጋቱ እንዳልተቀረፈ ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል።

በአንድ ግቢ ውስጥ ተደብቀው የሚገኙ ከ60 በላይ ሰዎች በጋራ ለኢሳት እንደገለጹት ሁኔታዎች አሁንም አስተማማኝ አይደሉም።

ከተማዋ ጭር በማለቷ አስፈሪ ድባብ እንዳለ ይናገራሉ። ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሱቆችና መደብሮች በመዘረፋቸው የሚበላና የሚጠጣ ለመግዛት የሚቻል እንዳልሆነ የሚገልጹት ነዋሪዎች በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንገኛለን ብለዋል።

ከዝርፊያ የተረፉ የተወሰኑ የንግድ ተቋማትም ዝግ በመሆናቸው በግዢ ምንም ነገር ማግኘት እንዳልተቻልም ገልጸዋል።

በቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ተጠልለው የሚገኙ ከ2ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ምግብና ውሃ ካጡ ቀናት አልፏቸዋል።

በተለይም ህጻናትና አዛውንቶች በረሃብ ምክንያት ለከፍተኛ አደጋ የተጋለጡ መሆናቸውን የገለጹት ነዋሪዎች የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ይድረስልን ሲሉ ጥሪ አድርገዋል።

አንጻራዊ የሆነ ሰላም በመስፍኑ ለጊዜው ህይወታችን ተርፏል፡ ነግር ግን በረሃብ ከማለቃችን በፊት ወገን ይድረስልን ብለዋል።- በተለያዩ ቦታዎች ተጠልለው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን።

ለኢሳት በደረሰው መረጃ ወደ ጂጂጋ ምግብ ለማድረስ ጉዞ የጀመሩ ተሽከርካሪዎች በታጠቁ ሃይሎች መንገድ ላይ በመታገታቸው የምግብና እህል አቅርቦት ለማድረስ አስቸጋሪ ሁኔታ ተፈጥሯል።

መንግስት ወደ ጂጂጋ የሚወስደውን መስመር ከአደጋ ነጻ በማድረግ ለተጎጂዎች እህል እንዲደርስ እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል።

አስቸኳይ የምግብና የእህል ድጋፍ ካልተደረገ የከፋ የሰብዓዊ ቀውስ ሊከሰት እንደሚችልም እየተነገረ ነው።

በሌላ በኩል የመከላከያ ሰራዊቱ ወደ ጂጂጋ መግባቱን ተከትሎ በተሳሳተ መረጃ ከተማዋን ትተው የሚወጡ የሶማሌ ክልል ተወላጆች እንዲመለሱ ጥሪ እየቀረበ ነው።

በዚሁ በተሳሳተ መረጃም የልዩ ሃይሉ ከመከላከያ ሰራዊቱ ጋር የተኩስ ልውውጥ ያደረገባቸው አካባቢዎች እንዳሉ የኢሳት የመረጃ ምንጮች ገልጸዋል።

በተያያዘ ዜና በደገሃቡር የመከላከያ ሰራዊት እንደገባ በመንግስት የመገናኛ ብዙሃን ቢነገርም፣ በፖሊስ ጣቢያ ተጠልለው የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች እንደተናገሩት ግን እስካሁኑ ሰዓት ድረስ አንድም የመከላከያ ሰራዊት ወደ ከተማው አልገባም።

የክልሉ ልዩ ሃይል አባላት አሁንም ርምጃ እንወስዳለን በማለት ህዝቡን እያስፈራሩ ነው።

ነዋሪዎቹ መከላከያ በፍጥነት እንዲገባላቸው እየተማጸኑ ነው።

እንደጂጂጋ ሁሉ በደገሃቡርና ቀብሪደሃር የሚገኙ ዜጎች ለከፍተኛ የምግብ እና የውሃ እጥረት መጋለጣቸውን ለኢሳት ገልጸዋል።