በጅግጅጋ አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን ነዋሪዎች ተናገሩ
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 01 ቀን 2010 ዓ/ም ) የመከላከያ ሰራዊት ከተማዋን ከተቆጣጠረ ከትናንት ጀምሮ አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን የገለጹት ነዋሪዎች፣ ቤቶቻቸው የተዘረፉባቸው እንዲሁም የሃይማኖት ተቋማት የወደሙባቸው ዜጎች በብስጭት ተቃውሞ ለማድረግ ቢያስቡም፣ የአገር ሽማግሌዎች በቀልን በበቀል መመለስ ትክክል አይደለም በማለት እንዳረጋጉዋቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል። የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ ሙሃመድ ከስልጣን የተነሱ ሲሆን ፣ በዛሬው እለት በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የአብዲ ኢሌ ታጣቂዎችና እርሱ ያደራጃቸው ሰዎች በወሰዱት እርምጃ በሶማሊ ተወላጆች ላይ የበቀል እርምጃ መውሰድ እንዲቆም፣ የአብዲ ኢሌን አገዛዝ በማጋለጥ እና በመቃወምሲተገል የቆየው አብዱላሂ ሁሴን ጥሪ አቅርቧል።
በሌላ በኩል ፕሬዚዳንቱ አብዲ ሞሃመድ ኡመር በቁጥጥር ስር ውለው፣ ጅግጅጋ ከሚገኘው ቤተ መንግሥት እንደተወሰዱ ቢቢሲ የአማርኛው ክፍል ዘግቧል። አህመድ አብዲ ሞሃመድ የቀድሞውን ፕሬዝዳንት በመተካት መሾማቸውን ይሁን እንጅ እርሳቸውም የአብዲ ኢሌ የቅርብ ሰው መሆናቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል።