“ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት በየትኛውም መንገድ ተቀባይነት የሌለው የሕዝብ ጠላትነት ተግባር ነው” ሲል ሰማያዊ ፓርቲ አስታወቀ
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 01 ቀን 2010 ዓ/ም ) በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በማንነት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች አስመልክቶ ሰማያዊ ፓርቲ ባወጣው መግለጫ ፤ “የኢትዮጵያ ሕዝብ የቁርጥ ቀን ልጆች በከፈሉት መራር መስዋዕትነት ባለፉት አራት ወራት አገራዊ አንድነት እና መግባባት፤ እንዲሁም የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት በአንፃራዊነት መከበራቸውን፤ የተጀመረው አበረታች ለውጥም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያንን ያሳተፈ እና ባለቤት ያደረገ ጭምር ነው” ብሎአል።
ይህን የለውጥ ጅማሮ ከመደገፍ እና ታሪካዊና አገራዊ አደራ ለመወጣት ከመትጋት ይልቅ በመንግስት ስልጣን እና ኃላፊነት ላይ ያሉ በአገራችን ኢትዮጵያ አልፎ አልፎ የብጥብጥና የሁከት ድርጊቶች እንዲቀሰቀሱ በማድረግ በዜጎቻችን ላይ ሰብዓዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት በማድረስ ህገወጥ ድርጊቶች እንዲስፋፋ ቀስቃሽ በመሆን ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር የጥፋት ሥራቸውን በማከናወን ላይ ይገኛሉ።
በጂግጂጋ ከተማ የተከሰተው ብጥብጥ የደረሰው ጉዳት በምንም መልኩ ተቀባይነት የሌለውና በአስቸኳይ ሊገታ የሚገባው ድርጊትና በማንአለብኝነት የተፈጠረ የጭካኔ ተግባር ነው። ከዚህ ቀደም በዜጎች ላይ የደረሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት በአለም አቀፍ ደረጃ እየታወቀ ምንም ዓይነት እርምጃ በአጥፊዎች ላይ አለመወሰዱ ለተጨማሪ ጥፋት ዳርጎናል ሲል ሰማያዊ ፓርቲ ለወንጀሉ መፈጸም በምክንያትነት ጠቅሷል።
ማንነትን መሰረት ያደረገው ጥቃት አብያተ ክርስቲያናትን ጭምር በማቃጠል ውድ የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት እየተቀጠፈ፣ ንብረት በጠራራ ፀሐይ ተዘርፏል፣ ይወድሟል። እንደዚህ ዓይነት ወንጀሎችና አስነዋሪ ድርጊቶች በሚፈፀሙበት ወቅት መስተዳድሩ ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት አልቻለም። ይልቁንም በአካባቢው የተቀሰቀሰው ግጭት መጠንና ዓይነቱን ጨምሮ ወደ ሌላው አካባቢ እንዲዛመትና ሐይማኖታዊ ቅርፅ እንዲይዝ በር እየከፈተ ይገኛል ሲል ወንጀሉን ኮንኗል።
በአካባቢው ለሚፈፀመው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት መጠየቅ ያለበት አካል በመንግስት ባለመጠየቁ ህገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ አስፈላጊውን እርምጃ በሚፈለገው ፍጥነት ባለመውሰዱ ከተጠያቂነት አይድንም ሲል ሰማያዊ ፓርቲ መግለጫውን ደምድሟል።