ኦነግ የተኩስ አቁም ስምምነት ተፈራረመ

(ኢሳት ዲሲነሃሴ 1/2010)  የኦሮሞ ነጻነት ግንባር /ኦነግ/ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት መፈራረሙ ተገለጸ።

ኦነግ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት በሰላማዊ መንገድ ትግሉን ለመቀጠል መስማማቱም ተመልክቷል።

ከኦሮሞ ነጻነትግንባር ጋር የሰላም ሥምምነት ለመፈራረም ወደ አስመራ ያቀኑት የኢትዮጵያ መንግስት ልኡካን  ከፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ጋር መወያየታቸውም ታውቋል።

ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር መሪዎች ጋር የሰላም ሥምምነት ለመፈራረም ትናንት ወደ ኤርትራ የተጓዙት  የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ  ከኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ እና ከሌሎች የኦነግ አመራሮች እንዲሁም ከሰራዊቱ አዛዥ ኮሎኔል ገመቹ አያና ጋር መወያየታቸውም ተመልክቷል።

በውይይቱ በተደረሰብት ሥምምነት መሰረት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ወደ ሃገር ቤት በመግባት ሰላማዊ ትግል የሚቀጥል ሲሆን ፣የተኩስ አቁም ሥምምነትም ተፈርሟል።

ዝርዝር አፈጻጸሙን የሚከታተል የጋራ ኮሚቴ  መቋቋሙም ተመልክቷል።የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ከአርባ አመታት  በፊት የተቋቋመ ሲሆን፣በ 1983 የደርግ ወታደራዊ መንግስት ሲወገድ የሽግግር መንግስቱ መስራች ነበረ።

የሽግግር ወቅቱን ቻርተር በማርቀቅ ሂደት የኦነግ ዋና ጸሃፊ የነበሩት  አቶ ሌንጮ ለታ ትልቅ ሚና እንደነበራቸውም ታውቋል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በሽግግሩ ምከር ቤት ከነበሩት 87 ወንበሮች 12 ቱን በመያዝ  ከሃገሪቱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች  አራቱን ሲመራም ቆይቷል።

ከህወሃት/ኢሕአዴግ ጋር  በከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ የቆየው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር /ኦነግ/ በአንድ  ዓመት ግዜ ውስጥ የሽግግር መንግስቱን ጥሎ በመውጣት የትጥቅ ትግሉን ቀጥሏል።

በወቅቱ የግንባሩ ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ገላሳ ዲልቦ  በአሁኑ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ሲተኩ ፣ዋና ጸሃፊ  የነበሩትን አቶ ሌንጮ ለታን ጨምሮ ጥቂት ያማይባሉ አመራሮች ከድርጅቱ ተሰናብተዋል።

አቶ ሌንጮ ለታ እና አንዳንድ አመራሮች ድርጅቱ ሲነሳ የያዘው የመገንጠል አጀንዳ እንዲከለስ ግፊት አድርገው ስላልተሳካላቸው ከድርጅቱ መልቀቃቸውም ተመልክቷል።

የኦነግ የመጀመሪያው ሊቀመንበር የነበሩት ዶ/ር ዲማ ኖጎ እንዲሁም የኦነግ ወሳኝ ሰው ተብለው የሚጠቀሱት የግንባሩ ዋና ጸሃፊ የነበሩት አቶ ሌንጮ ለታ እና ሌሎች የኦነግ አመራሮች ከድርጅቱ በመለየት የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር /ኦዴግ/ መስርተው  ሲንቀሳቀሱ   ቆይተዋል።

በቅርቡ በሃገሪቱ የተከሰተውን ለውጥ ተከትሎ  ወደ ሃገር ቤት መመለሳቸውም ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም  ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር መሪዎች ጋር የሰላም ሥምምነት ለመፈራራም ወደ ኤርትራ የተጓዙት አቶ ለማ መገርሳ እና ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂም ጋር መወያየታቸው ተዘግቧል ።

ውይይታቸው በምን ጉዳይ ላይ እንዳተኮረ ግን አልታወቀም።