በራያ አላማጣ እና ዋጃ አካባቢዎች የሚደርሱ ጥቃቶች መጨመራቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ
( ኢሳት ዜና ሃምሌ 10 ቀን 2010 ዓ/ም ) የትግራይ ክልል ልዩ ሃይል አባላት የጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ መስል ያለበትን ቲ ሸርት የለበሱ ሰዎችን እየያዙ በማሰር ላይ መሆናቸውን በአላማጣ ከተማ ከ300 በላይ ቲሸርቶችን ገዝቶ በማከፈፋሉ የተሳረው አቶ ሞገስ በላይ ለኢሳት ተናግሯል። በክልሉ ያሉ የፌደራል ፖሊሶች በያዙት ጊዜ የዶ/ር አብይን ቲሸርት ገዝተህ ለምን አከፋፈልክ ብለው እንደጠየቁት እርሱም ህዝብ ለሚወደውን መሪ፣ ገንዘብ ቢኖረኝ ከዚህ በበለጠ ገዝቼ አከፋፍል ነበር ብሎ መመለሱንና በዚህም ለ24 ሰዓታት ምግብና ውሃ ሳይገኝ ታስሮ መፈታቱን ገልጿል።
የልዩ ሃይል አባላቱ ዛሬ ሌሊትም እንዲሁ ተረፈ አርብሴ፣ አማረ ሴሩና ሞላ ዝናቤ እና ጥጋቡ የተባሉትን የአካባቢውን ተወላጆች ይዘው አስረዋል። ሰዎቹ ለዶ/ር አብይ ድጋፍ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የነበሩና መብታችን ይከበር በማለት ቅስቀሳ ሲያካሂዱ የነበሩ ናቸው።
የራያ ህዝብ የማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄ ጊዚያዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አገዘው ህዳሩ የሰዎችን መታሰር አረጋግጠው፣ ህዝቡም ልጆቻችን ካልተለቀቁ በሚል የአዲስ አበባ አስመራ መንገድ ዘግቶ መዋሉን ተናግረዋል። በራያ በኮረምና በአላማጣ ወረዳ ውጥረት መኖሩን፣ ዶ/ር አብይም በከፍተኛ ሁኔታ እየተወገዙ መሆኑን አቶ አግዘው ተናግረዋል።