ዶ/ር አብይ አህመድ መከላከያና ፌደራል ፖሊስ ችግር ባለባቸው አካቢዎች ጣልቃ እንዲገቡ አዘዙ
( ኢሳት ዜና ሃምሌ 9 ቀን 2010 ዓ/ም )ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ትዕዛዝ የሰጡት በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ ድንበር እየተባባሰ የመጣውን ግጭት ተከትሎ ነው። በቅርቡ በሶማሊ ክልልና ኦሮምያ ክልል ታጣቂዎች መካከል በተካሄደው ውጊያ በርካታ ዜጎች ተገድለዋል። ጦርነቱ በከባድ መሳሪያዎች ሳይቀር የታጀበ መሆኑ ብዙ ዜጎችን ስጋት ላይ ጥሏቸው ነበር። ይህን ተከትሎ እርምጃ አልወሰዱም በሚል ሲተቹ የነበሩት ጠ/ሚኒስትሩ ዛሬ ከፍ ያለ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። የመከላከያ ሰራዊትና የፌደራል ፖሊስ ግጭቶች ወዳሉበት ቦታ በመሄድ ግጭት እንዲያስቆም ማዘዛቸውን ተናግረዋል። በፌስቡክ ላይ ግጭቶች እንዲባባሱ የሚያደርጉ አክቲቪስቶች፣ ፖለቲከኞችና ሌሎች አካላት፣ ህዝብን ማጋጨት ያለፈበት ፋሽን መሆኑን ተረድተው ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጠ/ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የኤርትራውን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቄ ኢትዮጵያ በተገኙበት ወቅት የሶማሊ ክልል መሪ አብዲ ኢሌ እና የኦሮምያ ክልል መሪ ለማ መገርሳ በፕሬዚዳንቱ የአቀባባል ዝግጅት ላይ ተገኝተው ነበር። የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አህመድ ሺዴ፣ አቶ አብዲ እና አቶ ለማ ውይይት አድርገው የመከላከያ ሰራዊት እንዲገባ መስማማታቸውን ገልጸዋል።
አብዲ ኢሌ 1 ሚሊዮን ኦሮሞዎች እንዲፈናቀሉ ሲያደርግ፣ በሶማሊ ክልል በቅርቡ የታሰሩትን የፓርላማ አባል አቶ አብዲ አብዱላሂን ጨምሮ በርካታ ዜጎችን በኦጋዴን እስር ቤት አስሮ ሲያሰቃይ እስካሁን እርምጃ ባለመወሰዱ በርካታ የመብት ተቆርቋሪዎች ቅሬታቸውን እየገለጹ ነው። አቶ አብዲ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ በክልሉ ለደረሰው ጥፋት ሁሉ የቀድሞውን የደህንነት ሚኒስትር አቶ ጌታቸው አሰፋን ተጠያቂ አድርገው ነበር። ሂውማን ራይትስ ወችን ጨምሮ የተለያዩ የመብት ተሟጋቾች አቶ አብዲ ኢሌ ስልጣን እንዲለቁ እየጠየቁና ለፍርድ እንዲቀርቡ እየጠየቁ ነው።