የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቄ ላለፉት ሦስት ቀናት በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት አጠናቀው ዛሬ ወደ አስመራ ተመልሰዋል።

የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቄ ላለፉት ሦስት ቀናት በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት አጠናቀው ዛሬ ወደ አስመራ ተመልሰዋል።
( ኢሳት ዜና ሃምሌ 9 ቀን 2010 ዓ/ም )የኤትራው መሪ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ከሃያ ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።የኢትዮ-ኤርትራን የድንበር ግጭት ተከትሎ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በሀገራቱ መካከል ውጥረት ነግሶ ቆይቷል። ይህን ውጥረት ለማርገብ ሟቹ መለስ ዜናዊም ሆኑ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከመቶ ጊዜ በላይ ለኤርትራ ጥሪ ቢያቀርቡም ሊሳካላቸው እንዳልቻለ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ላለፉት መሪዎች የይምሰል ጥሪ ምላሽ ያልሰጠችው ኤርትራ ለዶክተር አብይ የሰላም ጥሪ ፈጣን ምላሽ ሰጥታለች። የሁለቱ ሀገራት እርቅና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ዓለምን ባስደነቀ መልኩ በፍጥነት ወደ ቦታው እየተመለሰ ነው። ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ ባለፉት ሦስት ቀናት በኢትዮጵያ የተደረገላቸው አቀባበል፣ ለዶክተር አብይ በኤርትራ ከተደረገላቸው አቀባበል ጋር የሚስተካከል ነው። በሁለቱም መሪዎች ጉብኝት ጎልቶ የወጣው አንድ እውነታ የሁለቱም ሀገራት ሕዝቦች ለሰላም፣ ለፍቅር፣አብሮ ለመኖርያላቸው ጉጉት ነው።
የኤርትራው መሪ አዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመን እና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት እና የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች አቀባበል አድርገውላቸዋል። የአማራው ክልል ርዕሰ መስተዳደር ገዱ አንዳርጋቸው በአቀባበል ሥነ ስር ዓቱ ላይ ያልተገኙት በዕለቱ ከሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የሚበረከትላቸውን የክብር ዶክትሬት ለመቀበል ወደዚያ በማቅናታቸው እንደሆነ ታውቋል።
አቶ ኢሳያስ ከቦሌ ተነስተው ቤተመንግስት እስኪደርሱ ድረስ የመዲናዋ ሕዝብ በመንገዶች ግራና ቀን በመሆን፣ በእልልታ እና በጭፈራና የእንኳን ደህና መጡ ደማቅ አቀባበል አድርጎላቸዋል። በሆነው ነገር ልባቸው የተነካ አንዲት እናት የጣት ቀለበታቸውን በማውጣት ለኤርራው ፕሬዚዳንት አበርክተዋል።
ዶክተር አብይ አህመድም ለሰላምና ለእርቅ ቃል ኪዳኑ ማሰሪያ ይሆን ዘንድ ቀለበቱን በአቶ ኢሳያስ ጣት አጥልቀዋል። ዕለቱኑ ከቀትር በኋላ የሀዋሳን ኢንደስትሪያል ፓርክ ለመጎብኘት ወደ ስፍራው ሲያቀኑ በሀዋሳ እና አካባቢው ሕዝብ እጅግ ደማቅ አቀባበል የተድረገላቸው ሁለቱ መሪዎች፣ከባህላዊ አልባሳት ጀምሮ ልዩ ልዩ ስጦታ ተበርክቶላቸዋል። እንደ አጀማመራቸው ፍጻሜያቸው ያምር ዘንድ መሬት ላይ ቁጢጥ ብለው በሀገር ሽማግሌዎች ተመርቀዋል። ከአንድ ማዕድ ጎርሰዋል።ከአንድ ጽዋ ጠጥተዋል። በቀለበት የታሰረው የሰላም ቃል ኪዳን በሽማግሌዎች ምርቃትና ከአንድ አቦሬ እንዲጠጡ በማድረግ እንዲጸና ተደርጓል።
ከዚህም ባሻገር የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳር አቶ ለማ መገርሳ የፈረስ፣ የሶማሌው ክልል ርዕሰ መሰተዳድር አቶ አብዲ ኢሌ የግመል ስጦታ አበርክተውላቸዋል።
በተደረገላቸ አቀባበል እና በሕዝቡ ስሜት ውስጣቸው የተነካው አቶ ኢሳያስ አፈወርቄ፦” ከእንግዲህ የኢትዮጵያን እና የኤርትራን ሕዝብ ሁለት ሕዝቦች እያሉ የሚጠሩ ሞኞች ናቸው።አንድ ሕዝብ ነን” ብለዋል።
ትናንት በሚሊኒየም አዳራሽ በተሰናዳው ልዩ የአቀባበል ሥነ ስርዓት ላይ የተገኘው ከሃያ አምስት ሺህ በላይ ሕዝብም ሁለቱ መሪዎች ወደ ሰላምና እርቅ ለመምጣት ላሳዩት ተነሳሽነትና ቅንነት አክብሮቱንና አድናቆቱን ገልጾላቸዋል።
የኤርትራው ፕሬዚዳንት ወደ ሥልጣን እስካሁን ድረስ በአማርኛ ሲናገሩ አለመታዬታቸው በአንዳድ ወገኖች ዘንድ ለቋንቋው ጥላቻ እንዳላቸው ተደርጎ ሲነገር መቆዬቱ ይታወሳል።
ቀደም ባሉት ዓመታት ስለዚህ ጉዳይ ተጠይቀው ቋንቋውን እንደሚያውቁ ፣ሆኖም በቃለ ምልልስ ወቅት የማይናገሩት የአማርኛ ንግግራቸው በመድረክና በአደባባይ ለማብራራት የሚያስችላቸው ስላልሆነ እንደሆነ መግለጻቸው ይታወሳል።
ትናንት በሚሊኒዬም አዳራሽ በአጭሩ ጽፈው በመምጣት ያደረጉትን ንግግር የተከታተሉ፣ ቀደም ሲል ያሉት ነገር እውነት መሆኑን እንዳረጋገጡ ሲገልጹ ተስተውለዋል።
እናም ፕሬዚዳንት ኢሳያስ፣የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን እና የኢትዮጵያን ሕዝብ ጥያቄ በማክበር ለመጀመሪያ ጊዜ በአማርኛ የሚከተለውን አሉ፦
“ክቡር የኢትዮጲያ ህዝብ ፣ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አሊ፣ የኤርትራን ህዝብ የሰላምታና የመልካም ምኞት ሳቀርብ የሚሰማኝን ደስታ እየገለጽኩ፣ እውን ስላደረጋችሁት ታሪካዊ ለውጥ እንኳን ደስ አላችሁ እላለሁ:: ያለፈውን ጥላቻ እና ውድመት ለመንዛት የተሞከረውን ሴራ አሸንፈን ለልማት፣ ለብልጽግናና ለመረጋጋት በሁሉም ግንባር አብረን ወደፊት ለመመረሽ ቆርጠን ተነስተናል:: ፍቅራችንንና ሰላማችን ለማወክ ፣እርጋታችንን ለማሸበርና ለማጥቃት፣ ልማትና እድገታችንን ለማደናቀፍና ለማውደም እንዲፈታተኑን ለማንም አንፈቅድም። በጋራ ጥረታችን የከሰርነውን አስመልሰን ለመጪ ግዜ ግዙፍ ሁኔታዎች ሰርተን እንደምናሸንፍ እርግጠኛች ነን። በድጋሚ ከባድ መስዋትነት ከፍላችሁ በኃይለኛ መስዋትነት ያስመዘገባችሁትን ድል እያሞገስኩ፣ ለዶክተር አብይ ብልህ አመራር ያለኝን ልባዊ ድጋፍና የድል ምኛት ደግሜ አረጋግጣለሁ አመሰግናለሁ”
“እርቅና ፍቅር የምር ሢሆን፣ እንዲህ ለሚያከብሩት መጨነቅ ይጀመራል”ብለዋል አስተያዬት ሰጭዎች።
የኤርትራው ፕሬዚዳንት ዛሬ ወደ አስመራ ከመመለሳቸው በፊት ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድና ከከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በመሆን ተዘግቶ የቆዬውን የሀገሪቱን ኤምባሲ ከፍተዋል።
የሁለቱ ሀገራት ግንኑነት ዳግም በጠንካራ መሰረት ላይ እየተጣለ መሆኑን ብዙዎች ያምናሉ።
“እኛ ተስማምተን በፍቅርና በአንድነት ከሠራን ከራሳችን አልፈን ለአፍሪቃ ቀንድና ለመላው አፍሪካ ጭምር እንተርፋለን” ብለዋል-ዶክተር አብይ አሕመድ።