ሕገወጥ የመሳሪያ ዝውውር ተጧጡፏል ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ /2010) ሕገወጥ የመሳሪያ ዝውውር በከፍተኛ ደረጃ እየተካሄደ መሆኑ ተገለጸ።

በአንድ ቀን ብቻ መትረየስን ጨምሮ 73 መሳሪያዎች ሰሜን ሸዋ ላይ መያዛቸውን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አስታውቋል።

የኦሮሚያ ክልል የገጠር ዘርፍ አደረጃጀት ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ እንዳስታወቁት 20 ሽጉጥና አንድ መትረየስ የጫነች የቤት ተሽከርካሪ ኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደብረሊባኖስ ወረዳ ላይ በቁጥጥር ስር ውላለች።

ትላንት መሳሪያ ጭና የተያዘችው ተሽከርካሪ ከደብረማርቆስ ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ላይ የነበረች መሆኑንም ተመልክቷል።

በተመሳሳይ በዚሁ ቀን 53 ሽጉጦችን ጭኖ ወደ አዲስ አበባ ሲጓዝ የነበረ አይሱዙ ተሽከርካሪ ሰሜን ሸዋ ዞን ቅምብቢት ወረዳ ላይ በቁጥጥር ስር መዋሉንም አቶ አዲሱ አረጋ ገልጸዋል።

በአጠቃላይ ሰሜን ሸዋ ዞን ላይ በአንድ ቀን 73 ሽጉጦችና አንድ መትረየስ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ሽጉጦቹን በምስል ማየት እንደተቻለውም ሩሲያ ስሪት ማካሮቭ መሆናቸው ታውቋል።

በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ከስልጣኑ ማዕድ የተገፉ ወገኖች እንዳቀነባበሩት የተገመተ ግጭት በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች መከሰቱ ይታወቃል።

ይህም ከዚሁ ጋር በተያያዘ ይሁን የተራ ንግድ የታወቀ ነገር የለም።