በዚገም ወረዳ በተነሳ ግጭት ወጣቶች ጉዳት ደረሰባቸው
( ኢሳት ዜና ሃምሌ 9 ቀን 2010 ዓ/ም )በአዊ ዞን በዚገም ወረዳ በጉምዝና በአገው ብሄረሰብ ተወላጆች መካከል ተነስቶ በነበረው ግጭት ከሁለቱም በኩል 9 ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ ህዝቡን ለማወያየት የመጡ 4 የዞን አመራሮች፣ ህዝቡ ከክልል አመራር ካልመጣና አጠቃላይ የወረዳውን ችግር ካላወያየን በሚል አመራሮቹን ለ3 ቀናት ያክል አስሮ ለፖሊስ በአደራ መልክ ያስረከበ ሲሆን፣ የታሰሩት አመራሮች ሌሊት ላይ በመለቀቃቸው ወጣቶች ወደ ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ ለማፈራረስ ሲሞክሩ በተተኮሰ ጥይት 4 ወጣቶች ተመተው አንዱ በቻግኒ ሆስፒታል፣ 3 ወጣቶች ደግሞ ባህርዳር ሪፈራል ሆስፒታል ተልከዋል። ህዝቡ ከ31 በላይ ፖሊሶችን ያሰረ ሲሆን፣ የልዩ ሃይል ወደ ከተማው መግባቱም ታውቋል። ከጤና ጣቢያ፣ ወፍጮ ቤትና ማህበራት በስተቀር ምንም አይነት የስራ እንቅስቃሴ የለም። ሁሉም የወረዳዉ አመራሮች ከተማውን ለቀው ቻግኒ ገብተዋል። ወረዳውን ህዝቡ የመረጣቸው ኮሚቴዎች እየመሩት መሆኑን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።