ኮለኔል ጎሹ ወልዴ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን የለውጥ ጉዞ እንደሚደግፉ ገለጹ

(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 14/2010) የቀድሞው መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ኮለኔል ጎሹ ወልዴ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን የለውጥ ጉዞ እንደሚደግፉ ገለጸ።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከጎናቸው እንዲሰለፍም ጥሪ አቅርበዋል።

“ዝምታዬን የሰበርኩት የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ራዕይ እንዲሁም የለውጥና የተሃድሶ አጀንዳ ለመደገፍና ኢትዮጵያውያን ወዳጆቼም እንዲደግፉት ለማሳሰብ ነው።”በማለት የ6 ደቂቃ የድምጽ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ኮለኔል ጎሹ ወልዴ እግዚአብሔር ግዜውን ጠብቆ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያጫቸውና የመረጣቸው ግለሰብ ናቸው ብዬም አምናለሁ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና በአሜሪካ ዬል ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያና 2ተኛ ዲግሪያቸውን ያገኙት ኮለኔል ጎሹ ወልዴ የቀዳማዊ ሃይለስላሴ ጦር አካዳሚ/ሐረር ጦር አካዳሚ/ ሁለተኛ ኮርስ ተመራቂ ናቸው።

በሕግ ተማሪነታቸው ወቅት ከአለም የሕግ ተማሪዎች ጋር /ሙት ኮርት/ በመወዳደር ያሸነፉና ከንጉሱ እጅ ሽልማት ከተቀበሉ ሶስት ኢትዮጵያውያንም አንዱ ነበሩ።

በደርግ ስርአት በተለያዩ የሃላፊነት ቦታዎች ያገለገሉትና በመጨረሻም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነታቸውን ስልጣን በፈቃዳቸው በመልቀቅ ከ30 አመታት በፊት የተሰደዱት ኮለኔል ጎሹ ወልዴ ኢሕአዴግ ወደ ስልጣን ሲመጣ መድህን የሚባል ድርጅት ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመመስረት ተሰሚነት የነበረው እንቅስቃሴ አድርገዋል።

ሆኖም ለረጅም አመታት ድምጻቸው ጠፍቶ የቆየውና ነዋሪነታቸውን በዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ የሆነው ኮለኔል ጎሹ ወልዴ ዝምታዬን ለመስበር ያስገደደኝ ሁኔታ ተከስቷል በማለት ድምጻቸውን አሰምተዋል።

“ዝምታዬን አቋርጬ በድንገት ብቅ ያልኩት የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ራዕይ እንዲሁም የለውጥና የተሃድሶ አጀንዳ ለመደገፍ ኢትዮጵያውያን ወዳጆቼም እንዲደግፉት ለማሳሰብ ነው”ብለዋል ኮለኔል ጎሹ ወልዴ።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድን በቴሌቪዥን ከማየት ውጭ የግል ትውውቅ እንደሌላቸውም አመልክተዋል።

“ነገር ግን የኢትዮጵያን ሁኔታ እንደተከታተልኩትና እንደገመገምኳቸው እግዚአብሔር ግዜውን ጠብቆ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መሪነት ያጫቸውና የመረጣቸው ግለሰብ ናቸው ብዬ አምናለሁ።”ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን በሳል፣ቆራጥና አንደበተ ርቱዕ በማለት የገለጹት ኮለኔል ጎሹ ወልዴ የለውጥና የተሃድሶ ርምጃዎቻቸው ገና በጅምር ላይ ያሉ ቢሆኑም ወደ ፖሊሲና ፕሮግራም ተቀይረው በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚሆኑ ተስፋቸውን ገልጸዋል።

የእስካሁኑ ጉዞም በራሱ ትልቅና ተጽእኖውም የጎላ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

ኢትዮጵያን ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንደሚያደርሷትም እምነቴ ነው ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዞ በኢትዮጵያውያን ላይ እየቀሰቀሰ ያለው የለውጥ፣የዲሞክራሲና የነጻነት ጥማት በኢትዮጵያ አኩሪ ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ክስተት ነው ማለት ይቻላል ብለዋል።

ኮለኔል ጎሹ ወልዴ እንደሚሉት ይህንን ራዕይና የለውጥ አጀንዳ ከመደገፍ፣ ከማበረታታትና ለተፈጻሚነቱም አብሮ ከመሰለፍ ውጪ ሌላ አማራጭ አይኖርም።

የመላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀልብ የሳበው ብሔራዊ አጀንዳና ራዕይ መቀልበስ ወይንም መደናቀፍ አስከፊ ውጤት ስለሚኖረውና ይህም እድል ተመልሶ ስለማይመጣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የለውጥ ጉዞ ጎን ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንዲሰለፍና እስከፍጻሜው አብሮ እንዲጓዝ ኮለኔል ጎሹ ወልዴ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ዝነኛው ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ በሳምንቱ መጀመሪያ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የለውጥ ጉዞ ድጋፉን መስጠቱም ይታወሳል።

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፣ፕሮፌሰር ጌታቸው ሃይሌ፣ፕሮፌሰር ጌታቸው በጋሻው፣ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያምን ጨምሮ በርካታ ምሁራን ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ድጋፍ መስጠታቸው ይታወሳል።

ዶክተር ነገደ ጎበዜ፣አቶ አበራ የማነአብ፣አቶ ክፍሌ ታደሰ፣ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ፣አቶ ብርሃኑ መዋ በይፋ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ድጋፍ ከሰጡ የፖለቲካ መሪዎችና ታዋቂ ሰዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ።