የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምህረት አዋጁን በቅርቡ ያጸድቃል ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 14/2010) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት  የምህረት አዋጁን በቅርቡ እንደሚያጸድቅ የፌዴራሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ገለጸ።

ምክር ቤቱ ለዕረፍት ከመበተኑ በፊት የምህረት አዋጁን ያፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቅላይ አቃቤ ህጉ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ  ገልጸዋል።

በሚኒስትሮች ምክርቤት ተመክሮበት ወደ ፓርላማው የተላከው አዋጅ በቀጣዮቹ ቀናት በፓርላማ ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ይሕንኑ ተከትሎም ተቋማቸው አዲስ አዋጅ እንደሚያዘጋጅ የፌዴራሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ገልፀዋል፡፡

ጠቅላይ አቃቤ ህጉ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ  እንዳሉት አዲሱ አዋጅ በሽብርተኝነት የተፈረጁ ግለሰቦችና ድርጅቶች ምህረት እንዲደረግላቸው የሚጠይቅ ነው።

አዲስ የሚዘጋጀው ይህ አዋጅ ተጠርጥረው በምርመራ ሂደት ያሉ ክስ የተመሰረተባቸው እንዲሁም የቅጣት ውሳኔ ለተላለፈባቸው ምህረት ማድረግንም ይመለከታል ብለዋል፡፡

እንዲህ አይነት ህግ መዘጋጀቱ በሃገሪቱ የለውጥ ጉዞ ውስጥ ለመሳተፍ ፍላጐት እያሳዩ ያሉና በፓርለማው በሽብርተኝነት የተፈራጁ እንደ ግንቦት ሰባት ያሉ ድርጅቶች ወደ ሀገራቸው ገብተው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንዲያደርጉ በር ይከፍታል ብለዋል፡፡

ቀደም ሲል በነበረው ሁኔታ ፓርላማው አሸባሪ ብሎ የፈረጃቸው 4 ድርጅቶች አርበኞች ግንቦት ሰባት፥የኦሮሞ ነጻነት ግንባር እንዲሁም የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር እና አልሻባብ እንደነበሩ ይታወሳል።

አርበኞች ግንቦት ሰባት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ለውጥ ወደ ዲሞክራሲ የሚያመራ ከሆነ የትጥቅ ትግሉን ሊያቆም እንደሚችል ትናንት ባወጣው መግለጫ ማስታወቁ ይታወሳል።