የተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያና ኤርትራን የሰላም ሂደት እደግፋለሁ አለ

(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 14/2010)የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኢትዮጵያና ኤርትራ ለጀመሩት የሰላም ሂደት ድጋፉን እንደሚያደርግ ገለጸ።

የመንግስታቱ ድርጅት ኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነታቸውን ለማሻሻል ለጀመሩት ስራ የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገለጿል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዩ ጉተሬዝ እንደገለጹት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነታቸውን ለማሻሻል የጀመሩት በጎ ስራ የሚደነቅ ነው ።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ  የሁለቱን ወንድማማች ሀገራት ግንኙነት ለማሻሻል ለጀመሩት ስራ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነታቸውን ለማሻሻል የጀመሩት ስራ በሁለቱ ሀገራት መካከል ሰላምን ከማስፈን በዘለለ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምም አወንታዊ ጠቀሜታ እንዳለውም አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ግልጸዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነታቸውን ለማሻሻል የጀመሩት ስራ ውጤታማ እንዲሆንም የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ዋና ፀሃፊው አስታውቀዋል።

ይሕ በእንዲሕ እንዳለም የተባበሩት መንግስታት በአዲስ አበባ ከተማ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድኝ በመደገፍ ግዙፍ ሰልፍ ሊካሂድ መሆኑን በመግለጽ በአካባቢው የሚገኙ ሰራተኞች እንዲያውቁት የምክር ደብዳቤ ጽፏል።

የአፍሪካ ህብረትም ኢትዮጵያና ኤርትራ በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል የተጀመሩትን በጎ ስራዎች ማድነቁ አይዘነጋም።

የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መሃመት፥ በሁለቱ ሀገራት መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሚደረገው ጥረት ግቡን እስኪመታ ድረስም ድጋፍ የሚደረግ መሆኑን አስታውቀዋል።