(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 14/2010) የኤርትራና የኢትዮጵያ ግንኙነት መሻሻሉ ለአፍሪካው ቀንድ ሰላም አስተዋጽኦው ከፍተኛ እንደሚሆን በጃፓን የኤርትራ አምባሳደር ገለጹ።
አምባሳደር እስጢፋኖስ አፈወርቂ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቆይታ ላይ እንደገለጹት ለ20 ዓመታት የዘለቀው የሁለቱ ሃገራት ፍጥጫ የሚያበቃበት ምዕራፍ ተጀምሯል።
ይህ ደግሞ ለአፍሪካው ቀንድ ሰላም ወሳኝ እንደሆነ አምባሳደሩ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ ልብ ናት ያሉት አምባሳደር እስጢፋኖስ ልብ ሲታመም ቀጠናው በሙሉ ይጎዳል። ኢትዮጵያ ሰላም ስትሆን ሁላችንም ሰላም እንሆናለን ብለዋል።
የኤርትራ መንግስት በኢትዮጵያ በኩል የቀረበውን ጥሪ በመቀበል ወደ አዲስ አበባ የልዑካን ቡድን እንደሚልክ ትላንት አስታውቋል።
በጃፓን የኤርትራ አምባሳደር እስጢፋኖስ አፈወርቂ በተለይ ለኢሳት እንደገለጹት የኤርትራ መንግስት በኢትዮጵያና በቀጠናው ያለውን የፖለቲካ ክስተት በቅርበት ከተከታተለ በኋላ ከውሳኔ ላይ ደርሷል።
በተለይ በኢትዮጵያ የሚታየው ለውጥ የኤርትራ መንግስትን ትኩረት መሳቡን የገለጹት አምባሳደር እስጢፋኖስ በቀጣይ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነትን የተመለከተ ውይይት ማድረጉ አስፈላጊ ሆኖ መወሰዱን ጠቅሰዋል።
አሁን የተጀመረው እንቅስቃሴ ለፍሬ እንደሚበቃም ነው አምባሳደር እስጢፋኖስ የገለጹት።
የብሔር ፖለቲካ ለኢትዮጵያ አደገኛ ነው በማለት የገለጹት በጃፓን የኤርትራ አምባሳደር በሁለቱ ሀገራት መካከል ግድግዳ ሆኖ የቆየው ጉዳይ አሁን እየተወገደ በመምጣቱ ለቀጣይ ኢኮኖሚያዊና ሌሎች ግንኙነቶች በጋራ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
በዶክተር አብይ የተጀመረው ሃገራዊ ስሜት ላይ ያተኮረው እንቅስቃሴ ለኢትዮጵያ መልካም እንደሆነ አምባሳደር እስጢፋኖስ ጠቅሰው ከእንግዲህ የአንድ ብሔር ላይ ያተኮረው ስርዓት ፍጻሜ መቃረቡ ለሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መሻሻል አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የአካባቢው ልብ ናት። ልብ ሲታመም አካባቢው በሙሉ ይታመማል ያሉት አምባሳደር እስጢፋኖስ ኢትዮጵያና ኤርትራ መደጋገፋቸው የግድ ነው ሲሉ አጽንኦት በመስጠት ገልጸዋል።