የኢትዮጵያ ልማት ባንክን ብድር መክፈል ያቆሙ ተበዳሪዎች ቁጥር ጨመረ

(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 13/2010) የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ያልተመለሰ እዳ ወይንም ብድሩንም ሆነ ወለዱን መክፈል ያቆሙ ተበዳሪዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩ ተገለጸ።

የመንግስት የፋይናንስ ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ስንታየሁ ወልደሚካኤል መሰብሰብ ያልቻለ ብድር 28 በመቶ ደርሷል ሲሉ ገልጿል።

የኢሳት ምንጮች ግን ያልተሰበሰበው የብድር መጠን 70 በመቶ መድረሱን አጋልጠዋል።

ይህ ደግሞ ባንኩ አደጋ ላይ እየወደቀ ለመሆኑ አመላካች ነው ተብሏል።

መንግስት ችግሩን ለመፍታትም የኢትዮጵያ ልማት ባንክን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ለማዋሃድ ማቀዱም ተመልክቷል።

ባለሙያዎች ይህ እቅድ ተግባራዊ ከሆነ ይበልጥ አደገኛ እንደሚሆን አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በብድር ካወጣው 40 ቢሊየን ብር 28 ቢሊየን ብሩ የመመለስ እድሉ ያከተመ መሆኑን የኢሳት ምንጮች ይገልጻሉ።

አብዛኛው ብድር በጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ለተሰማሩ ባለሃብቶች መለቀቁን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብድሩን ለማስመለስ አንዳንድ ፋብሪካዎቹን ከባለቤቶቹ ጋር በጋራ ማስተዳደር መጀመሩም ታውቋል።

በዚህ ረገድ የቱርክ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ተጠቃሽ ሆኗል። ፋብሪካው ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ የወሰደው 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ሲሆን ብድሩንም መመለሱ አጠራጣሪ ሆኗል።

ኢ ኤል ኤስ ኢ የተባለው የቱርክ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ስራውን ሲጀምር 1 ቢሊየን ብር ተበድሮ መሆኑም ታውቋል።

ነገር ግን ብድሩን መክፈል ሲያቅተው የፋብሪካው ባለቤቶች ከሃገር ወጥተዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፋብሪካውን በመሸጥ ገንዘቡን ለማስመለስ በተደጋጋሚ ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

በፋብሪካው የተገጠሙት ማሽኖች አሮጌና ያረጁ መሆናቸው ለሽያጩ እንቅፋት መሆኑም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሃብት ለከፍተኛ ብክነት የተጋለጠው የሕወሃት አባል የሆኑት አቶ ኢሳያስ ባህረ ልማት ባንኩን በመሩበት የ7 አመት ጊዜ ውስጥ እንደሆነም የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

አቶ ኢሳያስ ባህረ ከጋምቤላ እርሻ ኢንቨስትመንት ጋር በተያያዘ በአብዛኛው የሕወሃት አባላት ለሆኑ ግለሰቦች የ5 ቢሊየን ብር ብድር ሰጥተው ገንዘቡ ከባከነ በኋላ ከስልጣን ቢነሱም ሳይጠየቁ ከሃገር ወጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በአቶ ኢሳያስና በሌሎች ቀደምት የልማት ባንክ ሃላፊዎች ላይ ፌደራል ፖሊስ ምርመራ ጀምሯል።

ከፍተኛ የሃገር ሃብት ብክነት የታየበትና በንጉስ ሃይለስላሴ ዘመን መንግስት የተመሰረተው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከቀውስ እንዲወጣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር እንዲዋሃድ ዶክተር ስንታየሁ ወልደሚካኤል ሃሳብ ማቅረባቸው ታውቋል።

የመንግስት የፋይናንስ ተቋማት ዳይሬክተር ዶክተር ስንታየሁ ወልደሚካኤል ያቀረቡት ሃሳብ ተቀባይነት ካገኘ በሃገሪቱ ግዙፍ ተቋም በሚባለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ ችግር እንደሚያስከትል ባለሙያዎች ያሳስባሉ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከደንበኞቹ የሚቀበለውን የአጭር ጊዜ ተቀማጭ ሒሳብ ወደ ረጅም ግዜ ሊቀይረው ስለሚገደድ ችግር ያስከትላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኢትዮጵያ ልማት ባንክን ደርቦ የሚሰራ ከሆነም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከውጭ ባንኮች ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት የሚጎዳ መተማመንን የሚቀንስ እንደሆነም ያሳስባሉ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአሁኑ ወቅት ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን፣ለሜቴክ፣ለስኳር ኮርፖሬሽኖችና ለሌሎች ተቋማት የሚሰጠው ብድር ከ400 ቢሊየን ብር በላይ እንደሆነ ምንጮቹ ያስታውሳሉ።

ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን ውጭ ሌሎች ብድሩን መመለሳቸውም አጠራጣሪ መሆኑን ገልጸዋል።

ባንኩ እጅግ ከፍተኛ ብድር ባወጣበትና ብዙዎቹም እንደማይመልሱ በሚታመንበት በአሁኑ ወቅት ባንኩ ያልተመለሰ ብድር በማለት ያስቀመጠው አሃዝ 1 መቶኛ ብቻ ነው።

ሆኖም ይህ የተዛባ ቁጥር የሚሰጠው ባንኩ ጤነኛ ነው ለማለት  እንደሆነም ታውቋል።

በተጨባጭ ግን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያልተመለሱ ብድሮች መጠን 30 በመቶ መሆኑንም ምንጮቹ ይገልጻሉ።

ባለሙያዎች እንደሚሉት በሃገሪቱ የመንግስት ባንኮች ውስጥ ያለውን ችግር ለመፈተሽ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ አለም አቀፍ  ኦዲተሮችን ምርመራ እንዲያደርጉ መጋበዝ ይኖርባቸዋል።