ታህሳስ 19 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ፍርድ ቤቱ “አኬልዳማን” በተመለከተ እስረኞች ያቀረቡትን አቤቱታም ሳይቀበለው ቀርቷል።
አቃቢ ህግ ፣ የብሄራዊ የጸጥታና የደህንነት ቢሮ ህጋዊ በሆነ መንገድ የጠለፋቸው መረጃዎች ናቸው ያላቸውን 2 የኦዲዮ ማስረጃዎች በእስክንድር ነጋ ላይ አቅርቧል።
የኦዲዮ ማስረጃዎቹ እስክንድር ነጋ ከ16ኛ ተከሳሽ ከሆነው አበበ በለው ጋር ሲነጋጋር እንደነበር ያረጋገጣል ብሎአል።
አበበ በለው የግንቦት 7 ቃል አቀባይና የኢሳት የቦርድ አባል ነው ሲል አቃቢ ህግ ገልጧል።
ሁለቱ ተከሳሾች፣ “ኢሳት ጥሩ ስራ እየሰራ ስለመሆኑ፣ የግለሰቦችን ስም ሳይነኩ የተቃዋሚዎችን ስትራቴጂ መተቸት ተገቢ መሆኑን፣ ተቃዋሚዎች መስዋትነት ለመክፈል ቸልታ ማሳየታቸውን እና ይህን ወቅት ሊጠቀሙበት እንዳልቻሉ መነጋገራቸውን” አቃቢ ህግ ለፍርድ ቤቱ ገልጧል።
እስክንድር በፓልቶክ ውይይት ወቅት በካናዳ ከምትኖር ሴት ለቀረበለት ጥያቄ “ስለአረብ አብዮት፣ ስለኢሳት ስርጭትና ስለ ብሄር ፖለቲካ መናገሩን የሚያመልክት የኦዲዮ ማስረጃ መቅረቡንም” አቃቢ ህግ ጠቅሷል።
አቃቢ ህግ ቀሪዎቹ የኦዲዮ ማስረጃዎች በፍርድ ቤቱ ሳይቀርቡ ለተከሳሾች እንዲሰጣቸው የሚል ሀሳብ በማቅረቡ፣ ፍርድ ቤቱም ተቀብሎታል።
አቃቢ ህግ በተከሳሽ ነአምን ዘለቀ፣ አበበ ገላውና አበበ በለው ላይ ያስረዱልኛል ያላቸውን የሰነድ ማስረጃዎች ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል።
ተከሳሾች “በፍርድ ቤት በመታየት ላይ ባለ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ራዲዮ ፣ አኬልዳማ የሚል ድራማ በመስራት ተከሳሾችን ጥፋተኛ አድርጎ አቅርቧል” በማለት ላቀረቡት አቤቱታ፣ ፍርድ ቤቱ “ዝግጅቱ በፍርድ ቤት ሪፖርት ላይ ተመስርቶ ወይም አቃቢ ህግ ባቀረበው ማስረጃ ላይ ተንተርሶ የተዘጋጀ አይደለም” በሚል ምክንያት ውድቅ አድርጎታል።
በመጨረሻም በተከሳሾች ላይ ብይን ለመስጠት የሁለት ሳምንት የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቶ ተጠናቋል።