ኤርትራ፤”ገለልተኛ አይደለም”ያለችው የተባበሩት መንግስታት የሶማሊያ ጉዳይ አጣሪ ቡድን እንዲቀየር ጥያቄ አቀረበች

  20 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-

“በአዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት መሪዎች ስብሰባ ላይ የቦምብ ጥቃት ለማድረስ ሴራ ጠንስሳ ነበር” በሚል የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት አጣሪ ቡድን ያቀረበውን ሪፖርት እንደማትቀበለው በተደጋጋሚ መግለጿ ይታወሳል።

“ኤርትራ ፤የአጣሪ ቡድኑን  ሪፖርት ያልተቀበለችው፤ ፍትሃዊነት የሚጐድለውና በአድሎም የተሞላ ስለሆነ ነው” በማለት የየኤርትራ መንግስት   በአጣሪ ቡድኑ ላይ  ተቃውሞውን መግለጹም አይዘነጋም።

   በአዲስ መልክ የተጠናከረ የዲፕሎማሲ ዘመቻ መጀመሯ የሚነገረው ኤርትራ ፤ ሰሞኑን ለተባበሩት መንግስታት በላከችው ደብዳቤ ጉዳዩን የሚያጣራ አዲስ አጣሪ ቡድን እንዲቋቋም ጥሪ ማቅረቧን ሮይተርስ  ባሰራጨው ዘገባ ገልጿል።

የኤርትራ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያቤት ለፀጥታው ምክርቤት የላከውን ደብዳቤ እንዳገኘው የገለፀው ሮይተርስ፤ የኤርትራ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳለህ ለፀጥታው ምክርቤት የወቅቱ ሊቀመንበር  ለሩሲያዊው ቪታሊ ቹኪን በላኩት በዚህ ደብዳቤ፤ ቀደም ሲል የነበረው አጣሪ ቡድን፤ ገለልገኛ ያልሆነ፣ ነፃነት የሌለውና ሙያዊ ብቃትም የሚጐድለው በመሆኑ የፀጥታው ምክርቤት አዲስ አጣሪ ቡድን በማቋቋም የማጣራቱን ሥራ በድጋሚ እንዲጀምር መጠየቃቸውን ገልጿል።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ በዚሁ ደብዳቤያቸው ላይ የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት በሀገራቸው ላይ የጣለውን ማዕቀብ እንዲያነሳም መጠየቃቸውንም የዜና አውታሩ ጠቁሟል።

 የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ለ ኤርትራ መንግስት ደብዳቤ የሰጠው ምላሽ ይኑር አይኑር፤ የታወቀ ነገር የለም።