በአዲስ አበባ የጉርሻ ምግብ መሸጫ ቤቶች እየተስፋፉ ነው ተባለ

ታህሳስ 19 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ፎርቹን ጋዜጣ እንደዘገበው በአዲስ አበባ ከተማ አንድ እና ሁለት የነበሩት የጉርሻ ምግብ መሸጫ ቦታዎች በተለያዩ ክፍለ ከተሞችም እየተስፋፉ  ነው።

በመርካቶ ብቻ ሶስት የጉርሻ ምግብ መሸጫ ቦታዎች መኖራቸውን የዘገበው ፎርቹን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በፒያሳ፣ ስድስት ኪሎና ሌሎች ቦታዎችም የጉርጫ ምግብ መሸጫ ቦታዎች መቋቋማቸውን ዘግቧል።

ጉርሻ የሚባለው ከሆቴሎች የተረፈ ምግብ ወይም በተለምዶ “ቡሌ” ለአንድ ሰው አፍ በሚመጥን መልኩ በእጅ እየተመጠነ የሚሸጥ ምግብ ነው።

አንድ ጉርሻ ቡሌ ቀድሞ በ50 ሳንቲም ይሸጥ እንደነበር ያመለከተው ፎርቹን አሁን የተመጋቢው ቁጥር በመብዛቱና ኑሮም በመወደዱ አንድ ጉርሻ በ3 ብር በመሸጥ ላይ መሆኑን በፎቶግራፍ የተደገፈ ዘገባ ይዞ ወጥቷል።

በመርካቶ አካባቢ አንድ ምግብ በ15 ብር የሚሸጥ ቢሆንም፣ የቀን ሰራተኞች፣ ሊስትሮዎች፣ ተሸካሚዎች፣ እቃ አዙዋሪዎችና በልመና የሚተዳደሩ ሰዎች ይህን ያክል ገንዘብ መክፈል ስለማይችሉ፣ በጉርሻ ለመኖር ተገደዋል ይላል ጋዜጣው

የ24 አመቱ ፈቃዱ ጴጥሮስ ፣ አባቱ መሞታቸውን ተከትሎ ከወላይታ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት፣ የ7 ልጆች እናት የሆነችውን እናቱን የቀን ስራ እየሰራ ይረዳቸዋል። ፈቃዱ ለሚተኛበት መደብ በቀን 10 ብር ይከፍላል። በቀን ሁለት ጊዜ 6 ብር ከፍሎ ጉርሻ ምግብ ይመገባል። ከዚህ የተረፈውን ለቤተሰቡ እንደሚልክ ይናገራል።

“ጥሩ ጉርሻ ለማግኘት በጧት መሰለፍ ይጠይቃል” የሚለው ፈቃዱ፣ “ከሰአት በሁዋላ ከከሄደና ጉርሻ የሚያጎርሰው ሰው ክንድ ከዛለ በቂ ጉርሻ ማግኘት እንደማይቻል” ፈቃዱ ለጋዜጣው ዘጋቢ ገልጧል።

ቀድሞ በነጻ ይሰጥ የነበረው የሆቴል ትርፍራፊ ምግብ አሁን በፌስታል 30 ብር በመሸጥ ላይ መሆኑንም ጉርሻ በመሸጥ የሚተዳደረው ምህረተአብ ተወልደ ይናገራል።

በአሁኑ ጊዜ ጉርሻ ምግብ የመሸጥ ውድድር ውስጥ የገቡት ነጋዴዎች ፣ የእጅና የሚጠጣ ውሀ የሚያቀርቡ ከሆነ የተሻለ ትርፍ እንደሚያገኙ ጋዜጣው ዘግቧል።

በፈውስ ተራ አካባቢ ጉርሻ የሚገዙ ደንበኞች፣ ከበረካ ደሊል የቶታል ማደያ ውሀ በነጻ መጠጣት ስለሚችሉ የተሻለ ተጠቃሚዎች መሆናቸውንም ተገልጧል።

“11 በመቶ እድገት እንዳስመዘገበ፣ ህዝቡ በበቂ ሁኔታ እንዳለፈለት የሚናገረው የመለስ መንግስት”፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስፋፋ ስለመጣው የጉርሻ ሽያጭ እድገት የገለጠው ነገር የለም።

በአሁኑ ወቅት ከቀን ሰራተኛው በተጨማሪ የመንግስት ሰራተኞችም ወደ ጉርሻ ግዢ እየተሸጋገሩ መሆኑን መመልከት እንደሚቻል ጉርሻ ተጠቃሚዎች ይናገራሉ።

በአዲስ አበባ ምን ያክል ህዝብ ጉርሻ ተጠቃሚ እንደሆን ለማወቅ ባይቻልም፣ በከተማዋ ከሚገኘው 20 በመቶ  ስራአጥ ውስጥ ቢያንስ ከ10 በመቶ ያላነሰው በጉርሻ ምግብ ተዳዳሪ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።

በአንድ በኩል ጉርሻ ተመጋቢው በየጊዜው እያሻቀበ በሌላ በኩል ደግሞ ጥቂት ግለሰቦች በሀብት ላይ ሀብት እያካበቱ መምጣታቸው የኢትዮጵያ የቀን ተቀን ህይወት መገለጫ ሆኗል የሚሉ አስተያየቶች በብዛት ይቀርባሉ።

ግሎባል ፋይናንሻል ኢንተግሪቲ በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት በ2009 ብቻ ከኢትዮጵያ ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ተዘርፎ ወደ ውጭ ወጥቷል።

ባለፉት ሰባት አመታት ከአገሪቱ ተዘርፎ ወደ ውጭ የወጣው ገንዘብ ከ11 ቢሊዮን ዶላር በላይ መሆኑን ድርጅቱ መግለጡ ይታወሳል።