ህወሃት ጄ/ል ሳሞራ የኑስን በጄ/ል ሳዕረ መኮንን ለመተካት ግፊት እያደረገ ነው

ህወሃት ጄ/ል ሳሞራ የኑስን በጄ/ል ሳዕረ መኮንን ለመተካት ግፊት እያደረገ ነው
(ኢሳት ዜና ግንቦት 15 ቀን 2010 ዓ/ም) በኢህአዴግ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ሹም ሽር ተከትሎ ለረጅም አመታት የጦር ሃይሎች ኢታማዦር ሹም ሆነው የቆዩትን ጄ/ል ሳሞራ የኑስን በጄ/ል ሰዓረ መኮንን ለማስተካት ህወሃት ግፊት እያደረገ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል። በትግራይ ብሄርተኝነት ጽንፍ አቋም አላቸው የሚባሉት ጄ/ል ሰዓረ ኢታማዦር ሹም ሆነው የሚሾሙ ከሆነ፣ በኦህዴድና ብአዴን ዘንድ ተቀባይነት የማግኘቱ እድል አነስተኛ መሆኑን ምንጮች ይገልጻሉ።
ለውጥ ፈላጊ የሆኑ የኦህዴድና የብአዴን አባላት የመከላከያውን ስልጣን ተቆጣጥረው የያዙት የህወሃት ጄኔራሎች ተቀይረው ፍትሃዊ የሆነ የስልጣን ክፍፍል እንዲኖር ሲጠይቁ ቆይተዋል። ይሁን እንጅ የመከላከያ አዛዥነት ቦታውን ለመልቀቅ ፍላጎት የላሳየው ህወሃት፣ ጄ/ል ሳሞራ የኑስ ከእድሜና ከድካም ጋር በተያያዘ ይነሱ የሚለውን ሃሳብ ቢደግፍም፣ አዛዥነቱ ከእጁ እንዳይወጣ እየተከላከለ ነው። ጄ/ል ሳዕረ ለቦታው ብቁ መሆናቸውን እና ሌሎች የኢህአዴግ ድርጅቶችም ይህን እንዲቀበሉ ለማድረግ ግፊት የሚያደርገው ህወሃት፣ ከማእከላዊ ስልጣን እየተገፋሁ ነው በሚል ድጋፍ ለማግኘት እየጣረ ነው።
ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ በመከላከያ ውስጥ ለውጥ እንዲደረግ ፍላጎት እንዳላቸው ቢታወቅም፣ በጄ/ል ሳዕረ ሹመት ላይ ያላቸው አስተያየት ግልጽ አይደለም።