በቴፒ በሚካሄደው ተቃውሞ በርካታ ንብረት ወደመ

በቴፒ በሚካሄደው ተቃውሞ በርካታ ንብረት ወደመ
(ኢሳት ዜና ግንቦት 15 ቀን 2010 ዓ/ም) በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ በሾንጋ ግቢ ውስጥ ከሴት ተማሪዎች መደፈር ጋር ተያይዞ የተፈጠረው ተቃውሞ ወደ ሚዛን አማን ከተማ ተዛምቶ የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ ከፍተኛ ንብረት መዘረፉንና መውደሙን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
የግቢው ውሃ በሚጠፋበት ጊዜ ሴት ተማሪዎች ውሃ ለመቅዳት ወንዝ ሲወርዱ በአካባቢው ጎረምሶች በተደጋጋሚ እንደሚደፈሩ፣ ትናንት ደግሞ ሁለት ወንዶች አንዷን ተማሪ ወደ ሴቶች መታጠቢያ ቤት በመግባት ለመድፈር ሙከራ ማድረጋቸውን ተከትሎ ተማሪዎች ቁጣቸውን ለመግለጽ የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል።
ተቃውሞውን የሰሙ የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች አጋጣሚውን በመጠቀም የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል። ወጣቶቹ የተለያዩ የመብትና የኢኮኖሚ ጥያቄዎችን ሲያሰሙ ከቆዩ በሁዋላ፣ በአካባቢው ለርጅም አመታት በኖሩ መጤ ባሉዋቸው ብሄረሰቦች የንግድ ድርጅቶች ላይ ዝርፊያ መፈጸማቸው ታውቋል። በአካባቢው በርካታ የአማራ ተወላጆች የሚኖሩ ሲሆን፣ ብዙዎቹ የንግድ ድርጅቶቻቸው ተዘርፎባቸዋል።
አንዳንድ ነዋሪዎች የመብትና የኢኮኖሞ ጥያቄው ወደ ብሄር ግጭት እንዲዞር ለማድረግ የአስተዳዳሪዎችና በአካባቢው የሰፈሩ ባለሀብቶች እጅ አለበት ይላሉ።በኢትዮ-አግሪ የተያዙ የበበቃ ሰፋፊ የእርሻ የቡና እርሻ ማሳዎች፣ በባለስልጣናት የተያዙ በጉራፈርዳና ሌሎችም አካባቢዎች የሚገኙ ሰፋፊ የእርሻ ቦታዎች ስራ አጥቶ ለሚንከራተተው የከተማው ወጣት እንዲሰጡ ወጣቶች ጥያቄ አቅርበዋል። አካባቢው በተፈጥሮ ሃብት የታደለ ቢሆንም፣ ጥቂት ባለስልጣናት የአካባቢውን መሬት ዘርፈው ሃብት እያፈሩ ወጣቱን ለስራ አጥነትና ለችግር መዳረጋቸውን ነዋሪዎች ይናገራሉ። የመሰረተ ልማት ችግሮችም ለተቃውሞው አንዱ መንስኤ መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ።
እንዲሁም ጉዳያቸውን ለማስፈጸም የክልሉ ዋና ከተማ ወደሆነው ወደ አዋሳ 1 ሺ ኪሜትሮች መጓዝ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጉዳት እያደረሰባቸው በመሆኑ፣ የከፋ ዞን 3 ብሄረሰቦች፣ የቤንች ማጂ ዞን 6 ብሄረሰቦች ፣ የሸካ ዞን 3 ብሄረሰቦች ፣ የመንጃንና ሌሎችንም 13 ብሄረሰቦች ጨምሮ አንድ ክልል እንዲሆንና አዋሳ ከመመላለስ እንዲድኑ ጥያቄ ያቀርባሉ። የአካባቢው ባለስልጣናት ጥያቄውን አፍነው መቆየታቸው አሁን ለተፈጠረው ችግር ዋና ምክንያት መሆኑነ ነዋሪዎች ይናገራሉ።
መከላከያ ወደ አካባቢው በመግባት በህዝቡ ላይ ድብደባ ማካሄዱን ነዋሪዎች ገልጸዋል።