በሶማሌ ክልል 11 ሰዎች ተገደሉ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 8/2010) በሶማሌ ክልል በቀጠለው ተቃውሞ በፊቅ ዞን በሁለት ከተሞች 11 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ። ኢሳት የተገደሉት ሰዎች ስም ዝርዝር ደርሶታል።

ፋይል

ቡሳ እና ለጋሂዳ በተባሉ ከተሞች ግድያውን የፈጸሙት የክልሉ ልዩ ሃይልና ሚሊሺያ ታጣቂዎች መሆናቸው ታውቋል።

ልዩ ሃይሉ ከየከተሞቹ እንዲወጣ ከፌደራል መንግስት ትዕዛዝ መሰጠቱን የሚጠቅሱት የኢሳት ምንጮች በህወሃት ጄነራሎች የሚደገፈው የክልሉ ፕሬዝዳንት ትዕዛዙን ተግባራዊ ለማድረግ እንዳልፈለገ ገልጸዋል።

አንደኛ ወሩን እየደፈነ ያለው የሶማሌ ክልሉ ተቃውሞ የንጹሃንን ግድያ እያስከተለ መሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎች በመውጣት ላይ ናቸው።

ባለፈው ሳምንት በቀብሪዳሃር የአንዲት ወጣት ግድያ በክልሉ የተጀመረውን ህዝባዊ ተቃውሞ እንዲጠናከር ማድረጉን ነው ለማወቅ የተቻለው።

የአብዲ ዒሌ አስተዳደር ከስልጣን እንዲወርድ በመጠየቅ እየተካሄደ ባለው ተቃውሞ እንደትላንት በርካታ ሰዎች የተገደሉበት ክስተት ከዚህ ቀደም አልተመዘገበም።

በፊቅ ዞን ሁለት ከተሞች የተካሄደውን ተቃውሞ ለማስቆም የተሰማሩት የአብዲ ዒሌ ታጣቂዎች 11 ሰዎች መግደላቸውን በስም ዝርዝር በተደገፈ መልኩ ለኢሳት የደረሰው መረጃ አመልክቷል።

ግድያው የተፈጸመው የፌደራል መንግስቱ የአብዲ ዒሌ አስተዳደር በየከተሞቹ ያሰማራቸውን የልዩ ሃይል አባላትን ወደ ጂጂጋ እንዲመልሳቸው ትዕዛዝ በተሰጠበት ማግስት እንደሆነም ይነገራል።

በጨካኝነቱ የሚታወቀውና በአብዲ ዒሌ የሚታዘዘው ልዩ ሃይል  በሰሞኑ ተቃውሞ የሃይል ርምጃ በመውሰድ በእስከአሁን ወደ 20 የሚጠጉ የሶማሌ ተወላጆችን መግደሉም ታውቋል።

አቶ አብዲ ዒሌ የፌደራል መንግስቱን ትዕዛዝ ባለመቀበል የልዩ ሃይል ታጣቂዎች በየከተሞቹ ርምጃ በመውሰድ እንዲቀጥሉ ማድረጋቸው አነጋጋሪ ሆኗል።

በህወሀት ጄነራሎች የሚደገፉት አቶ አብዲ ዒሌ የፌደራል መንግስቱን ትዕዛዝ ላለመቀበላቸው የሰጡት ምክንያት እንደሌለ ነው ከምንጮች ዘገባ ለማወቅ የተቻለው።

ትላንት በፊቅ ዞን ቡሳና ለጋሂዳ በተባሉ ከተሞች የተገደሉት 11 ሰዎች የተጀመረውን ተቃውሞ ሊያባብሰው እንደሚችል ነው የኢሳት የመረጃ ምንጮች የሚገልጹት።

በከተሞቹ የተነሳውን ተቃውሞ በሀይል ለመቀልበስ የተሰማሩት የልዩ ሃይልና የሚሊሺያ ታጣቂዎች ህዝቡ ላይ በቀጥታ መተኮሳቸውን የአይን እማኞች ገልጸዋል።

ሌሎች በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውም ታውቋል። ከተገደሉት መሀል ዘጠኙ ሴቶች መሆናቸውንም በስም ዝርዝር ለኢሳት ከተላከው መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ሶስት ሰዎች እንደሚገኙበት የተገለጸ ሲሆን ግድያው ሆን ተብሎ የተፈጸመና ሰዎቹን ዒላማ አድርጎ የተከናወነ ሊሆን እንደሚችልም ተገልጿል።

በሁለቱ ከተሞች ዛሬም ውጥረት መንገሱን የሚያሳዩ መረጃዎች እየወጡ ነው።

ትላንት ጀምሮ እስከዛሬ በጂጂጋ አቅራቢያ ባሉት ሁለት መንደሮች ተቃውሞ እየተካሄደ መሆኑንም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በተለይም ደገህሌይ በተባለች መንደር ህዝቡ አደባባይ በመውጣት የአብዲ ዒሌ አስተዳደር ከስልጣን እንዲወርድና ገዳይ የሆኑትን ታጣቂዎች ከአካባቢያቸው እንዲያስወጣ ጠይቀዋል።

በአብዲ ዒሌ ላይ እየተካሄደ ያለው ተቃውሞ በክልሉ 11ዱም ዞኖች የተዛመተ ሲሆን በእስካሁኑ ሒደት 20 ሰዎች ተገድለዋል። ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች ታፍነው ተወስደዋል።

ተቃውሞ በዓለም ዙሪያ በሶማሌ ኮሚኒቲ ማህበረሰብ በመከናወን ላይ እንደሆነም ታውቋል።