የሞቱ ፍልስጤማውያን ቁጥር 58 ደረሰ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 7/2010) ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ኤምባሲዋን ወደ ኢየሩሳሌም ናዛወሯን ተከትሎ በተነሳው ተቃውሞ የሞቱ ፍልስጤማውያን ቁጥር 58 ደረሰ።

በተቃውሞው ጉዳት የደረሰባቸው ፍልስጤማውያን ቁጥርም 2ሺ 700 ደርሷል።

በተቃውሞው ሳቢያ ተጨማሪ  ዕልቂት እናዳይፈጠር ስጋት ደቅኗል።

ፍልስጤማውያን ምስራቃዊው የኢየሩሳሌም ክፍል የነገዋ የፍልስጤም ሃገራቸው ርዕሰ ከተማ እንደሚሆን በመናገር  ላይ ባሉበት በአሁኑ ወቅት የአሜሪካ ኤምባሲ ትናንት በኢየሩሳሌም  መከፈቱ ለግጭቱ መከሰት ምክንያት ሆኗል።

አሜሪካ በሁለቱ ወገኖች ዘንድ የሸማጋይነት ሚና ስትጫወት ከቆየች በኋላ ፣በአዲሱ የሜሪካ ፕሬዚዳንት ውሳኔ አሜሪካ ኢምባሲዋን ከቴላቪቭ ወደ ኢየሩሳኤም ማዛወሯ ከተማዋ የእስራኤል ናት  የሚል ምስክርነት ተደርጎ በመታየቱ ፍልስጤማውያን ትናንት  በቁጣ አደባባይ እንዲወጡ አድርጓቸዋል።

የዛሬ 70 ዓመት እስራኤል እንደ ሃገር ስትመሰረት ፍልስጤማውያንን በማፈናቀል ነው  በሚል  “ናካባ” የሚሉትን የማፈናቀል ቀን እያስታወሱ ባሉበት ወቅት የአሜሪካ ኤምባሲ ኢየሩሳሌም ውስጥ መከፈቱ ለተቃውሞው መበርታት አስተዋጾ ማድረጉ ተመልክቷል።  የፍልስጤም ባለስስልጣናት እንደተናገሩት በግጭቱ 58 ፍልስጤማውያን ሲገደሉ፣2ሺህ 700 የሚሆኑ ደግሞ ቆስለዋል።ዛሬ የሟቾቹ ቀብር ተፈጽሟል።