በአማራ ተወላጆች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት እንደቀጠለ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 8/ 2010) በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በአማራ ተወላጆች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት መቀጠሉ ተገለጸ።

በመተከል ሁለት የአማራ ተወላጆች በጫካ ተገድለው መገኘታቸውን የኢሳት ወኪል ከስፍራው ካደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

የአማራ ክልል መንግስት ከጥቃት ሸሽተው በቅርቡ ወደ ባህርዳር የተሰደዱ የአማራ ተወላጆችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ ጥረት እያደረገ ባለበት በአሁኑ ወቅት ግድያው መቀጠሉ ተነግሯል።

ባለፈው ህዳር ወር የጀመረው ጥቃት አሁንም ቀጥሏል።

ከቀዬ መንደራቸው በማንነታቸው ተለይተው ጥቃት እየተሰነዘረባቸው የሚገኙት የአማራ ተወላጆች ከወራት የስጋት ኑሮ በኋላ ወደ ባህር ዳር ሽሽት ቢመጡም የቀሩ ዘመድ ወገኖቻቸው ከጥቃት ሊያመልጡ አልቻሉም።

ከ1ሺህ በላይ የአማራ ተወላጆች ባህርዳር በስደት የገቡበት ሁኔታ ተቃውሞና ቁጣ እያስነሳ ባለበት በዚህን ወቅት ተጨማሪ ጥቃት በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን በሚገኙ የአማራ ተወላጆች ላይ መፈጸሙን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ከትላንት በስቲያ ግንቦት 6 ቀን 2010 ዓ.ም በድባጢ ወረዳ ዝግህ ቀበሌ ውስጥ አበጥር ወርቁ  የተባለ የ14 ዓመት ታዳጊ በተደራጁ የከባቢው ተወላጆች በስለት ተወጋግቶ ፡ የቀኝ አይኑ ጥፍቶ ጥለውት መሄዳቸው ታውቋል።

ታዳጊው አበጥር በህይወትና በሞት መካከል ሁኖ በፖዊ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገለት ይገኛል።

ይህን የፈጸሙት የአከባቢው ተወላጆች በክልሉ ፖሊስና ሚኒሻ  አማካኝነት እንዲሸሹና ወደ ጫካ እንዲገቡ መደረጋቸውም ታውቋል።

ከዚያ ቀደም ብሎ ግንቦት 5 ቀን 2010 ዓ.ም በማንቡክ ወረዳ ወደ ጉብላክ ቀበሌ በሚወስደው መንገድ ቁጥር 3 ተብሎ በሚጠራ ስፍራ ላይ አንድ የአማራ ተወላጅ ሹፌር ህጻን ልጅ ገጭተሃል ተብሎ ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሞበት በህይወትና ሞት መሃል ሆኖ ፓዌ ሆስፒታል እንደገባ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

የአአከባቢው ተወላጆች በዚህ ሳያበቁ ከእርሻ የሚመለሱ ባልናሚስት የሆኑ የአማራ ተወላጆችን በጫካ ውስጥ  በአሰቃቂ ሁኔታ መግደላቸውን ለማወቅ ተችሏል።

በቤንሻንጉል ጉምዝ በአማራ ተወላጆች ላይ እየተፈጸመ ያለው ጥቃት የግልሰቦች ጸብ ነው በሚል በክልሉ ባለስልጣናት እየተሰጠ ያለው ማስተባበያ ከእውነት የራቀ መሆኑን ያጋለጠ አንድ ደብዳቤ ሰሞኑን ሾልኮ መውጣቱ የሚታወስ ነው።

በወረዳ አስተዳደር ተጽፎ የወጣው ደብዳቤው የአማራ ተወላጆች ቀነ ገደብ ተቀምጦላቸው ከክልሉ በአስቸኳይ እንዲለቁ የሚያስገድድ ሲሆን ይህን ባያደርጉ ለሚደርስባቸው ማንኛውም ጉዳት ተጠያቂ እንደማይሆን የሚገልጽ ነው።

ይህም የአማራ ተወላጆች ጥቃት በመንግስት ትዕዛዝና እውቅና የሚደረግ ለመሆኑ እንደማስረጃ የሚታይ ነው ተብሏል።

በስደት ባህር ዳር የገቡትን የአማራ ተወላጆችን ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ ግፊት እየተደረገ ባለበት በዚህን ወቅት ነው ተጨማሪ ጥቃት እየተፈጸመ ያለው።