(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 7/2010)አቶ ስብሃት ነጋን ጨምሮ 5 የሕወሃት እና የኢሕአዴግ አመራር የነበሩ ባለስልጣናት ከመንግስት ሓላፊነታቸው በጡረታ ተገለሉ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ትዕዛዝ በጡረታ ከተገለሉት ባለስልጣናት መካከል ዶ/ር ካሱ ኢላላን ጨምሮ ሁለቱ ከፖሊሲ ምርምር እና ጥናት ማዕከል መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።
የብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የህወሃቱ ዘርዓይ አስገዶምም ከስልጣናቸው ተባረዋል።
ከአቶ መለስ ዜናዊ በፊት የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ /ሕወሓት / ሊቀመንበር የነበሩት የ83 ዓመቱ አዛውንት አቶ ስብሃት ነጋ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስር ባለው የሰላም እና ጥናት ምርምር ኢንስቲቱት ዋና ዳይሬክተር በመሆን በማገልገል ላይ ነበሩ፡
የሃገሪቱ ሕግ ከ65 ዓመት በላይ በመንግስት ስራ ላይ መቀጠለን ባይፈቅድም አቶ ስብሃት ግን ይህን የሃላፊነት ስፍራ የያዙት ከ75 ዓመታቸው በኋላ ነበር።ለዓመታት በሕወሃት ውስጥ ሲካሄድ በነበረው ሽኩቻ የአንደኛው ቡድን መሪ መሆናቸው የሚገለጸው አቶ ስብሃት ነጋ ቡድናቸው በሕወሓት ውስጥ አሸናፊ በመሆን የአቶ አባይ ወልዱን እና እና የወ/ሮ አዜብን ቡድን ቢያባርርም እንደታሰበወ በመጡበት መንገድ የሕወሃትን የበላይነት ለማስቀጠል ያደርጉት ሙከራ አልተሳካም።
የዴኢህዴኑን አቶ ሽፈራው ሽጉጤን የኢሕአዴግ ሊቀመንበር በማድረግ በፖለቲካውም ውስጥ ህወሃት የበላይነቱን ለማስጠበቅ ያደረገው ሙከራ ኦህዴድ እና ብአዴን በመቀናጀት የከፊል ደኢህዴኖችን ድጋፍ በማግኘት እንዳከሸፉት ሲዘገብ ቆይቷል።
አቶ ስብሃት ነጋ በልጃቸው ተከስተ ስብሃት እና በበርካታ የቤተሰቦቻቸው አባላት ከፍተኛ ሙስና ውስጥ ከተሰማሩ የሕወሃት ባለስልጣናት አንዱ መሆናቸው ይጠቀሳል።
ሆኖም በስማቸው ይህ ነው የሚባል ሃብት አለመመዝገቡንም የቅርብ ምንጮች ይገልጻሉ።
ከአቶ ስብሃት ነጋ በተጨማሪ በጡረታ የተሸኙት ሌላው ባለስልጣን የዴኢህዴኑ ድ
ዶ/ር ካሱ ኢላላ ናቸው ፣ለሕወሃት ሰዎች ፍጹም ታማኝ መሆናቸው የሚገለጸው ዶ/ር ካሱ ኢላላ ኢሕአዴግ አዲስ አበባ ሳይገባ በኢሕዴን አማካይነት ኢህአዲግን ተቀላቅለዋል።
ኢህዴን ወደ ብአዴን ሲዞር ወደ ደቡብ ድርጅት ወደ ደኢህዴን የተዛወሩት ካሱ ኢላላ እስከ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስር ማዕረግ ስርዓቱን ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
የንግድ ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ታደሰ ሃይሌ ሌላው በጡረታ የተሸኙ ባለስልጣን ሲሆኑ ፣በደርግ ዘመን የኢሰፓ አባል፣በኢሕዴግ ዘመን ደግሞ የሕወሃት አባል በመሆን ማገልገላቸው ተመልክቷል።አራተኛው በጡረታ የተሸኙት አቶ መኮንን ማንያዘዋል የኢሕአዴግን ስርዓት አባል ሳይሆኑ ከሚያገለግሉ ጥቂት ባለሙያዎች አንዱ መሆናቸው ይጠቀሳል።በፖሊሲ ምርምር እና ጥናት ተቋም ውስጥ ሲያገልግሉ ቆይተዋል።አቶ በለጠ ታፈረ የተባሉ ባለስልጣንም በጡረታ ከተሸኙት ውስጥ አንዱ ሆነዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የኢትዮጵየብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘርዓይ አስገዶም ከሃላፊነታቸው ተነስተው በምትካቸው አቶ ሰለሞን ተስፋዬ የተባሉ የደኢሕዴን አባል መሾማቸው ተዘግቧል።ባለፈው ሳምንት ግንቦት 2ቀን 2010 ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለአቶ ሰለሞን ተስፋዬ የተጻፈው ደብዳቤ
“በአዋጅ ቁጥር 533/1999 አንቀጽ 12/1 መሰረት ከግንቦት 1 ቀን 2010 ጀምሮ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙ መሆኑን አስታውቃለሁ “ የሚል እንደሆነም በመገኛኛ ብዙሃን ከተሰራጩ መረጃዎች ች መረዳት ተችሏል።የብሮድ ካስት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ልኡል ገብሩን በተመለከተ የታወቀ ነገር የለም።የብሮድካስት ባለስልጣን ዋና እና ምክትል ዳይሬክተርነት እንዲሁም የቦርድ ሰብሳቢው ጭምር የህወሃት አባላት ናቸው።