የባለስልጣናት አካውንቶች ላይ ምርመራ እየተደረገ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 7 /2010) በውጭ አገራት ባንኮች አካውንት ያላቸው ባለስልጣናት በአካውንቶቻቸው ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ።

ዶክተር አብይ አህመድ በጽህፈት ቤታቸው ለተሰበሰቡ የተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በስራዎቻቸው ዙሪያ ገለጻና ማሳሰቢያ ሰጥተዋል ።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በዚህ መድረክ ላይ የራሳቸውን ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል። በዚሁ ጽሁፋቸውም የአመራር ጥበብን በተመለከተ ገለጻ ማድረጋቸው ነው የተገለጸው ።

የህዝብ አገልጋይ ምን አይነት ሰብዕና ሊላበስ እንደሚገባ አገልግሎት ሲሰጥም በምን አይነት ጊዜና ቦታ መሆን እንዳለበትም በተለያዩ አብነቶች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በውጭ አገራት ባንኮች አካውንት ያላቸው ባለስልጣናት በአካውንቶቻቸው ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑንና ለዚህም አገራት ትብብር እያደረጉ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ገለጻቸው ወቅት እንዳሉት ሳምንታዊው የካቢኔ ስብሰባ ከአርብ ወደ ቅዳሜ ተዛውሯል። ሚኒስትሮች አርብ በስብሰባ ስም ጊዜ ማባካን እንደሌለባቸውና መደበኛ ስራቸውን እንዲሰሩ በማሳሰብ።

ኢትዮጵያ አድጋለች ከማለት ባሻገር በተጨባጭ ህዝቡ ምን ያህል ተጠቅሟል የሚለውን መፈተሽና ማረጋገጥ አለብን ሲሉም ዶር አብይ ገልጸዋል።

እያንዳንዱ የመንግስት አመራርም አሰራሩን ግልጽና ለህዝብ የማይደበቅ ማድረግ እንደሚገባውም ዶክተር አብይ አሳስበዋል።

እያንዳንዱ ሚኒስትር ከዚህ በኋላ ለስብሰባ ሲመጣ በቂ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ሚኒስትር ሃሳብ አመንጪ እንጂ አቃቂር አውጭ አይደለም” ሲሉም ነው አጽንኦት የሰጡት።

ጠቅላይ ሚኒስተሩ ከስብሰባው በሁዋላ ባለስልጣናቱን ከአዳራሽ ይዘው በመውጣት በአጼ ሚኒሊክ፣ በአጼ ኃይለሥላሴ እና በደርግ ዘመን የተለያዩ ታሪካዊ ድርጊቶች የተፈጸሙባቸው በቤተመንግስት የሚገኙና እስካሁን ድረስ ዝግ የነበሩ የተለያዩ ክፍሎችን አስከፍተው እንዲጎበኟቸው አድርገዋል።

በዚህም ባለስልጣናቱ የነገስታቱን የግብር ቤቶች፣ አጼ ሀይለስላሴ የተገደሉበትን፣ የደርግ ጄኔራሎች የተረሸኑባቸውን ክፍሎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነት ጎብኝተዋል።