በእስራኤል ጋዛ ድንበር በተነሳ ተቃውሞ 37 ሰዎች ተገደሉ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 6/2010) አሜሪካ ኤምባሲዋን ወደ ኢየሩሳሌም ማዛወሯን ተከትሎ በተነሳ ተቃውሞ 37 የሚሆኑ ፍልስጤማውያን ተገደሉ።

በጋዛ ድንበር የእስራኤል ወታደሮች በከፈቱት ተኩስ ከ1 ሺ 3 መቶ በላይ ፍልስጤማውያን መቁሰላቸውም ታውቋል።

አሜሪካ ዛሬ ቢሮዋን በይፋ ከቴላቪቭ ወደ ወደ ኢየሩሳሌም ማዛወሯን ተከትሎ በሚደረገው የመክፈቻ ዝግጅት ላይ ለመገኘት የአሜሪካ ባለስልጣናት ኢየሩሳሌም መግባታቸው ታውቋል።

ባለፈው ታህሳስ ወር ነበር የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለእስራኤሏ ኢየሩሳሌም እውቅና የሰጡት።

ፕሬዝዳንቱ በዚህ ብቻ ሳያበቁ ለኢየሩሳሌም እውቅና ማጠናከሪያ ነው ያሉትንና መቀመጫውን በቴላቪቭ ያደረገውን ኤምባሲያቸውን ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚያዛውሩ ይፋ ያደረጉት።

ዛሬ ቀኑ ደርሶ አሜሪካ ኤምባሲዋን በይፋ ወደ ኢየሩሳሌም ታዛውራለች።ለዚህም ባለስልጣኖቿን ወደ ስፍራው ልካለች።

ይህን ተከትሎም በጋዛ ውጥረት ነግሷል።

እስካሁንም በጋዛ ድንበር ላይ የእስራኤል ወታደሮች ከፈቱት በተባለው ተኩስ ይሄ ዜና እስከተጠናቀረበት ድረስ 41 ፍልስጤማውያን ተገድለዋል ከ1 ሺ 8መቶ በላይ ቆስለዋል።

የህንን የአሜሪካ ውሳኔ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚስትር ለእስራኤል እውቅና ያሰጠ ታሪካዊ ውሳኔ ነው በማለት አወድሰውታል።

ሌሎችም ሀገራት ይህንን  ተከትሎ ለምስራቅ ኢየሩሳሌም እውቅና ይሰጥ ሲሉ ጥያቄ ማቅረባቸው ተሰምቷል።

የአውሮፓ ህብረት ግን የአሜሪካ ውሳኔ ሊዋጥለት አልቻለም። አሁንም ተቃውሞውን በማሰማት ላይ ነው።

እስራኤል ምስራቅ ኢየሩሳሌምን እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ1967 ጀምሮ ይዞታዋ ብታደርግም ለዚህ ይዞታዋ ግን አንድም ሀገር እውቅናን ሊሰጣት አልቻለም ይላል ቢቢሲ በዘገባው።

እናም ዛሬ በይፋ ከቴላቪቭ ወደ ኢየሩሳሌም የሚዛወረውን የአሜሪካ ኤምባሲ ዝግጅት በመቃወም ከ35ሺ በላይ የሚሆኑ ፍልስጤማውያን ለተቃውሞ አደባባይ ወተዋል።ከእስራኤል ወታደሮች ጋርም ተጋጭተዋል።

እስካሁንም 41 ፍልስጤማውያን ሲገደሉ ከ1 ሺ 8 መቶ በላይ ቆስለዋል።

እንደ ዘገባው ከሆነ የሟቾቹም ሆነ የተጎጂዎቹ ቁጥር ከዚህም በላይ ሊያሻቅብ ይችላል።