ከኢትዮጵያ 1 መቶ ሺህ የሚጠጉ ዜጎች በየአመቱ እንደሚፈልሱ ታወቀ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 1/2010)በኢትዮጵያ እየተፈጸመ ባለ ሰቆቃና የኑሮ ውድነት ውጣውረድ 1 መቶ ሺህ የሚጠጉ የሃገሪቱ ዜጎች በየአመቱ ቀይባህርን ተሻግረው እንደሚፈልሱ ተነገረ።

ፋይል

ግሎባል ዴቨሎፕመንት የተባለን ተቋም ጠቅሶ ዘጋርዲያን እንደዘገበው ከፍልሰተኞቹ መካከል አብዛኞቹ ከኦሮሚያ ክልል የተሰደዱ ናቸው ።

ከኢትዮጵያ እየፈለሱ በጅቡቲ በኩል ቀይባህርን የሚሻገሩ ስደተኞች ከሆነላቸው ወደ አውሮፓ ካልቀናቸው ደግሞ ሳውዲ አረቢያን የሚያልሙ ናቸው።

በዙዎቹ አስቸጋሪውን በርሃ እና ባህር ሲሻገሩ ሕይወት ከማጣት ጀምሮ የተለያዩ ችግሮች እንደሚደርስባቸው ግሎባል ዴቨሎፕመንት የተባለው ተቋም ገልጿል።

የጅቡቲ ፖሊስ እንደሚለው ከሆነ ከኢትዮጵያ ወደ ዚችው መሸጋገሪያ ሃገር በየቀኑ 200 ኢትዮጵያውያን ድንበር ተሻግረው በድብቅ ይገባሉ።

ባለፈው የካቲት ብቻ አለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት አይ ኦ ኤም እንዳረጋገጠው 17ሺ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በጅቡቲ መዝግቧል።

እነዚሁ ፍልሰተኞች ታዲያ አቦክና ታጁራ በተባሉ የቀይ ባህር ዳርቻ ከተሞች ወደ የመን ለመሻገር የተዘጋጁ ናቸው ተብሏል።

ከነዚሁም መካከል ሁለት ሶስተኛዎቹ ወንዶች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ሴቶች ናቸው።

እናም ግሎባል ዲቨሎፕመንትን ጠቅሶ ዘጋርዲያን እንደዘገበው በየአመቱ ብቻ 1 መቶ ሺ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ቀይ ባህርን ይሻገራሉ።

ከነዚሁ ፍልሰተኞች መካከልም አብዛኞቹ ከኦሮሚያ ክልል የተሰደዱ ናቸው ተብሏል።

ፍልሰተኞቹ ወደ የመን፣ሳውዳረቢያና አውሮፓ በቀይ ባህር በኩል ብዙ ውጣ ውረድ አልፈው የሚሰደዱት በኢትዮጵያ የሚፈጸምባቸውን ሰቆቃ ለመሸሽና በኑሮ ውጣ ውረድ ምክንያት መሆኑን ዘጋርዲያን ዘግቧል።