የብአዴን ጉባኤ በከፍተኛ ውዝግብ መቀጠሉ ተሰማ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 1/2010) በባህርዳር የተጀመረው የብአዴን ጉባኤ በከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ መቀጠሉን ምንጮች ገለጹ።

በእነ አቶ በረከት ስምኦን ግፊትና ተጽእኖ ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት የተባረሩ ተመልሰው በተሳተፉበት በዚህ ኮንፈረንስ ለውጥ ፈላጊዎቹ እነ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የበላይነት እያገኙ መምጣታቸው ተመልክቷል።

ቅዳሜ ሚያዚያ 27/2010 የተጀመረው ይህ የብአዴን ኮንፈረንስ መልካም አስተዳደር፣መርህ አልባ ግንኙነት፣የትራንስፎርሜሽን እቅድ ውጤታማነት የሚሉና ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩ አቅጣጫ ተቀምጦ ነበር።

አቅጣጫው የተቀመጠው ደግሞ በአቶ በረከት ስምኦን፣በአቶ አለምነው መኮንንና በሌሎች የቡድኑ አባላት መሆኑ ታውቋል።

የስብሰባው አቅጣጫም ሆነ አጀንዳ በፈለጉት መንገድ ያልሔደላቸው አቶ በረከት ስምኦንና ተከታዮቻቸው ወደ ዘለፋና ዛቻ ቢያመሩም አልተሳካላቸውም ተብሏል።

እንዲያውም ከተሰብሳቢው የአጸፋ ምላሽ እንደተሰጣቸው ታውቋል።

የትግራይ የበላይነት የሚለውን አጀንዳ አንዳንዶች የሕወሃት ተስፋፊነት ሲሉ መግለጻቸው ተመልክቷል።

በብአዴን ውስጥ የተፈጠረው ክፍፍል ከመጥበብ ይልቅ እየሰፋ ከመቀጠሉ ባሻገር ዝቅተኛው ካድሬ ለእነ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ግልጽ ድጋፍ ማሳየቱ በሕወሃት ሰዎችም ዘንድ ቁጣ መቀስቀሱ ተሰምቷል።

በዚህም ከአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጎን የተሰለፉትን ለማሸማቀቅ በሕወሃቱ አቶ ጌታቸው አሰፋ የሚመራው የደህንነት መስሪያ ቤት ሰላዮቹን በብዛት ባህርዳር አካባቢ ማሰማራቱ ታውቋል።

ከስብሰባው በኋላም በአንዳንዶቹ ላይ ክትትል እያደረጉ የማስፈራራት ስራ በመስራት ላይ መሆናቸው ተመልክቷል።

ለድርጅቱ ነጻነትና ለክልሉ ሕዝብ መብት በሚል ድምጽ የሚያሰሙትን ብረት ካነሱ ሃይሎች ጋር በማገኛነት የማስፈራራት ስራዎችም መቀጠላቸው ተሰምቷል።

እነ አቶ በረከት በስብሰባው አዳራሽ የሚያደርጉት ግፊትም ሆነ የደህንነት መስሪያ ቤቱ ማስፈራሪያ የስብሰባውን ሒደት መለወጥ አልቻለም።

የወልቃይትን ጉዳይ በማንሳታቸውና መሰል የመብት ጥያቄ በማቅረባቸው ከድርጅቱ የተባረሩና ወደ ተራ አባልነት ዝቅ የተደረጉ ሰዎችም በእነ አቶ ገዱ ግፊት ወደ ድርጅቱ እየተመለሱና ወደ አመራርነት ደረጃ እየወጡ መሆናቸው ታውቋል፥ኮንፈረንሱ በውጥረት ቀጥሏል።