ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የተደረሰውን ስምምነት አፈረሱ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 1/2010) የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ከኢራን ጋር ዩራኒየም በማበልጸግ ዙሪያ የደረሰችውን ስምምነት ማፍረሳቸውን አስታወቁ።

የኢራኑ ፕሬዝዳንት ሃሰን ሩሃኒ ጉዳዩን በስምምነቱ ውስጥ ስላሉት ሃገራት ስንል እናጤነዋል ሲሉ የሃገሪቱ መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ አሊ ካምኒ ግን ስምምነቱን ለማስቀጠል በሃገራቱ ላይ እምነት የለኝም ሲሉ እቅጩን ተናግረዋል።

በስምምነቱ ውስጥ ያሉት ሃያላን ሃገራት መሪዎችን ግን ጉዳዩ ያበቃለት አይደልም ብለዋል።

እንደ አውሮፕያኑ አቆጣጠር በ 2015 ነበር ኢራንን ጨምሮ አምስት በኢኮኖሚ የበለጸጉ ሀገራት በኢራን ዩራኒየም የማበልጸግ ሂደት ላይ ከስምምነት የደረሱት።

ይህን ስምምነት ከፈረሙት መካከል የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ አንዱ ናቸው።

ዛሬ ላይ ደግሞ ተተኪያቸው  ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኦባማ የተፈረመውን ስምምነት የማስቀጠሉ ሂደት ላይ እምነት የለኝም ሲሉ ተናግረዋል።

ከጅምሩም ስምምነቱ ትክክል አይደለም ያሉት ትረምፕ ሂደቱን እንደማያስቀጥሉ በግልጽ አስቀምጠዋል።

የትራምፕን ድንገተኛ ውሳኔም ተከትሎ የፈረንሳዩ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ጄን-ያቪስ ላ ድሬን  ስምምነቱ ትራምፕ ካስቀመጡት ውሳኔ ጋር ተያይዞ ይፈርሳል የሚል እምነት የለኝም ብለዋል።

አሜሪካ ከስምምነቱ ብትወጣም ስምምነቱ ግን እንደሚቀጥል በእርግጠኝነት ተናግረዋል።

ቢቢሲ እንደዘገበው የዶናልድ ትራምፕን ውሳኔ ተከትሎ የኢራኑ ፕሬዝዳንት ሃሰን ሩሃኒ ሌሎቹ ሀገራት እስካሉ ድረስ የአሜሪካ መውጣት የዩራኒየም ማበልጸግ ሂደቱን ስምምነት አያስተጓጉለውም  ይቀጥላል ብለዋል።

የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ አሊ ካሚኒ ግን አሜሪካንን ከጅምሩም አናምናትም ሌሎቹ ሀገራት ላይም ቢሆን እምነት የለኝም ሲሉ እቅጩን ተናግረዋል።

ሩሲያ በትራምፕ ውሳኔ መቆጣትዋን ስትገልጽ ቻይና ደግሞ አዝኛለሁ ብላለች።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታኒያሁ ግን ከዚህ ምስቅልቅል ካለ ስምምነት አሜሪካ እራሱዋን ማግለልዋ በሳል ውሳኔ ነው ሲሉ አሞካሽተውታል።