(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 18/2010) የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽነር ዛይድ ራድ አል ሁሴን የኢትዮጵያ መንግስት የሰብአዊ መብትን በማክበር ለዜጎች ተስፋ እንዲሰጥ ጠየቁ።
ኮሚሽነሩ በኢትዮጵያ ያካሄዱትን ጉብኝት ካጠናቀቁ በኋላ በሰጡት መግለጫ አዲሱ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ አመራር ለሕዝቡ የሰጠውን ተስፋ በመተግበር የሰብአዊ መብቶች ሊጠበቁ ይገባል ብለዋል።
በጉብኝታቸውም የፖለቲካ እስረኞች የነበሩ ሰዎችን፣ የሃይማኖት አባቶችንና ባህላዊ መሪዎችን አነጋግረው ሕዝቡ በአዲሱ አስተዳደር የተገቡ ተስፋዎች መክነው እንዳይቀሩ ስጋት እንዳላቸው መረዳታቸውን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽነር ዛይድ ራድ አልሁሴን የአገዛዙ ባለስልጣናትን ካነጋገሩ በኋላ በኦሮሚያና በአዲስ አበባ የፖለቲካ እስረኛ የነበሩትንና የሃይማኖት እንዲሁም ባህላዊ መሪዎችን አነጋግረዋል።
በመጀመሪያው ጉብኝታቸው በኦሮሚያና አማራ ክልሎች ጉብኝት እንዲያደርጉ ተከልክለው የነበሩት ኮሚሽነሩ በአሁኑ 2ኛ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ገደቡ ተነስቶ ወደ ቢሾፍቱና መሰል አካባቢዎች ከነዋሪዎች ጋር መወያየታቸው አዎንታዊ ርምጃ መሆኑን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።
በዚሁ ውይይታቸውም ዜጎች በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ንግግሮችና በሰጧቸው ቃል ኪዳኖች ተስፋ መሰነቃቸውን እንደተረዱ ነው የተናገሩት።
ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ጋር ባካሄዱት ውይይትም ለግጭት ምክንያት የነበሩ የፍትሕ እጦቶችን ለማስተካከል መንግስታቸው ቁርጠኛ መሆኑን እንደተገነዘቡም ገልጸዋል።
መንግስትን በመቃወማቸውና በመተቸታቸው ታስረው የነበሩ ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች ከእስር መፈታታቸው አዎንታዊ ርምጃ እንደሆነም ኮሚሽነር ዛይድ ራድ አልሁሴን በመግለጫቸው ተናግረዋል።
እናም ከእስር የተለቀቁ ሰዎችንና ልዩ ልዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለማነጋገር መቻላቸውን ነው የገለጹት።
በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ አባገዳዎችን ሲያናግሩም በሃገሪቱ ያለውን ችግር በግልጽ በማውራት በመንግስት የተፈጸሙ በደሎችን እንደዘረዘሩላቸው ተናግረዋል።
ኮሚሽነሩ ከአባ ገዳዎች ጋር ሲወያዩ የክልል ባለስልጣናት የነበሩ ቢሆንም ሰዎቹ ግን ችግሩን ከመናገር አልተቆጠቡም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን አባ ገዳ በየነ ሰንበቶ በእሬቻው እልቂት ጉዳይ ላይ የጸጥታ ሃይሎች ሰው አልገደሉም የሚል ምስክርነት እንዲሰጡ ተገደው እምቢተኛ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል።
በተለይ ከሰብአዊ መብት ጠበቃ ከሆኑ ሁለት የአለም አቀፍ ተወካዮች ጋር በሮዝሜሪ የተካሄደው ውይይት በመንግስት ባለስልጣናት ትዕዛዝ እንዲቋረጥ መደረጉ ተነግሯል።